እስራኤል ከሃማስ ጋር እያደረገችው ያለው ጦርነት ከ51 ቢሊየን ዶላር በላይ ያስወጣታል ተባለ
ቴል አቪቭ በየቀኑ በጋዛ ለምታዘንበው ቦምብ ከ1 ቢሊየን ሸክልስ (250 ሺህ ዶላር) እንደምታወጣም ነው ካልካሊስት የተሰኘው የእስራኤል ጋዜጣ የገለጸው
እስራኤል በጋዛ ጦርነት የምታወጣው ወጪ ከሀገራዊ ጠቅላላ ምርቷ (ጂዲፒዋ) 10 በመቶውን እንደሚይዝም ተገምቷል
እስራኤል በጋዛ ከሃማስ ጋር የጀመረችው ጦርነት ከ51 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚያሳጣት ተነገረ።
ካልካሊስት የተሰኘው የፋይናንስ ጉዳዮችን የሚሸፍን የእስራኤል ጋዜጣ እንዳስነበበው ጦርነቱ እስራኤልን 200 ቢሊየን ዶላር ሸክልስ ያስወጣታል።
ጋዜጣው የሀገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስቴር ቅድመ ግምትን ዋቢ አድርጎ ይዞት በወጣው ዘገባ፥ ጦርነቱ ከ8 እስከ 12 ወራት ድረስ ከዘለቀ እስራኤል ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርቷ (ጂዲፒዋ) 10 በመቶውን ለጦርነቱ ለማዋል ትገደዳለች ብሏል።
ግምቱ ጦርነቱ በጋዛ ከሃማስ ጋር ብቻ የሚካሄድ ይሆናል በሚል ታስቦ የወጣ ነው የሚለው ካልካሊስት፥ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ፣ ኢራን እና የመን በቀጥታ ተሳትፎ ማድረግ ከጀመሩ ግን ወጪው ከዚህም እጅግ የናረ እንደሚሆን አብራርቷል።
ጋዜጣው ከ350 ሺህ በላይ ተጠባባቂ ሃይሎች የእስራኤል ጦርን ይቀላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስነብቧል።
ካልካሊስት ጋዜጣ ከ51 ቢሊየን ዶላር ወጪው ውስጥ ግማሹ ለወታደራዊ ወጪዎች ይውላል ብሏል።
እስራኤል በየቀኑ 1 ቢሊየን ሸክልስ (250 ሺህ ዶላር) ታወጣለች ተብሎ እንደሚገመትም ገልጿል።
ከ17 እስከ 20 ቢሊየን ሸክልስ ለወደሙ የንግድ ድርጅቶች ካሳ ይከፈላል፤ እስከ 20 ቢሊየን ሸክልስ ደግሞ ለመልሶ ማቋቋም ስራዎች ይውላል የሚል ግምት ተቀምጧልም ነው ያለው።
የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛለል ስሞትሪች በሃማስ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው እስራኤላውያን የኮቪድ ወረርሽኝ ተከስቶ በነበረበት ወቅት ከተደረገው የተሻለ የድጋፍ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል ማለታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም ጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ቀላል ባይሆንም ለተጎጂዎች ፈጣን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ ተደምጠዋል።