እስራኤል የሃማስን ዋነኛ የጦር ካምፕ መቆጣጠሯን አስታወቀች
በሰሜናዊ ጋዛ ጃባሊያ የሚገኘውን የሃማስ ካምፕ ለመያዝ 10 ስአት የፈጀ ከባድ ውጊያ መደረጉንም ነው የሀገሪቱ ጦር ያስታወቀው
እስራኤል በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ ላይ በፈጸመችው የአየር ድብደባ በርካታ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ተብሏል
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ የሃማስን ዋነኛ የጦር ካምፕ መቆጣጠሯን አስታወቀች።
በምዕራባዊ ጃባሊያ የሚገኘው የሃማስ ካምፕ 10 ስአት ከወሰደ ከባድ ውጊያ በኋላ በእስራኤል ጦር በቁጥጥር ስር መዋሉንም ጦሩ በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ አስፍሯል።
“ናሃል” የተሰኘው ብርጌድ ከሃማስ ታጣቂዎች ነጻ ያደረገው የጦር ካምፕ የቡድኑ ዋነኛ ይዞታ የሚባል መሆኑንም ጠቅሷል።
በዚህ ዘመቻ በርካታ የሃማስ ታጣቂዎች መገደላቸውና የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውን የእስራኤል ጦር በመግለጫው አመላክቷል።
ሃማስ ከመዋዕለ ህጻናት አቅራቢያ የቆፈረውና ወደ ረጅም ዋሻ የሚመራ ጉድጓድ ማግኘታቸውንም ነው የጠቆመው።
የእስራኤል ጦር “በምድር ላይ እና በምድር ውስጥ” ውጊያ ስለማድረጉም በመግለጫው አመላክቷል።
10 ስአት ወስዷል በተባለው ውጊያ በሁለቱም ወገን ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ አልተጠቀሰም።
የእስራኤል ጦር የሃማስን ቀጣይ ወታደራዊ እቅዶች የሚያመላክቱ ሰነዶችን ማግኘቱን አስታውቋል፤ ምንም እንኳን ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ቢቆጠብም።
ሃማስ “አውትፖስት 17” የተሰኘው ወታደራዊ ጣቢያው በእስራኤል ጦር ተይዟል መባሉን እስካሁን አላስተባበለም።
የፍልስጤም ዜና አገልግሎት ዋፋ የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በጃባሊያ ድብደባ ሲፈጸሙ ማደራቸውን ዘግቧል።
እስካሁንም በጥቂቱ 14 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ እና በርካቶች መቁሰላቸውንም ነው የጠቀሰው።