ከአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያገኙ ሀገራት
አሜሪካ በፈረንጆቹ 2023 በዩኤስኤአይዲ በኩል 44 ቢሊየን ዶላር እርዳታ ለተለያዩ ሀገራት ለግሳለች
ኢትዮጵያ ከአሜሪካው የእርዳታ ድርጅት ከ1.67 ቢሊየን ዶላር በላይ አግኝታለች
የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የተመሰረተው በፈረንጆቹ 1961 ነው።
35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የቀዝቃዛው ጦርነት ውጥረት ከፍታ ላይ በደረሰበት ወቅት ዩኤስኤአይዲን ያቋቋሙት በውጭ እርዳታ ስም የያኔዋን ሶቪየት ህብረት ተጽዕኖ ለመቀነስ በማለም ነበር።
ድርጅቱ ከሶቪየት መፈራረስ በኋላም በመላው አለም ለሚሊየኖች ድጋፍ እያደረገ የአሜሪካ አለማቀፍ ተጽዕኖ መፍጠሪያ መሳሪያ ሆኖ 64ኛ አመቱን ይዟል።
የአለማችን ቀዳሚዋ የእርዳታ ለጋሽ ሀገር አሜሪካ በ2023 ለተለያዩ ሀገራት የ68 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን የሀገሪቱ መንግስት መረጃ ያሳያል። ከዚህ ውስጥ 44 ቢሊየን ዶላሩ በአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በኩል የቀረበ ነው።
አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር የውጭ እርዳታን ለ90 ቀናት እንዲቋረጥ ሲያዙ ዩኤስኤአይዲም በአሜሪካ መንግስት ስር እንደገና እንዲደራጅ ውሳኔ አሳልፈዋል።
የድርጅቱ ድረገጽ ተዘግቶም ሰራተኞች በዋሽንግተን ወደሚገኘው ዋና ቢሮ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ዳግም ተዋቅሮ ስራ እንደሚጀምር የሚጠበቀው የተራድኦ ድርጅቱ በ2023 ከፍተኛ ድጋፍ ካደረገላቸው ሀገራት ዩክሬን በቀዳሚነት ተቀምጣለች።
ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ሶስተኛ አመቷን ለመያዝ የተቃረበችው ኬቭ በድርጅቱ በኩል የ16 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ተደርጎላታል።
ከ20 ሚሊየን በላይ ዜጎቿ የምግብ ድጋፍ የሚሹባት ኢትዮጵያ ከአሜሪካው የእርዳታ ድርጅት ከ1.67 ቢሊየን ዶላር በላይ አግኝታለች።
የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ሀገራት ከድርጅቱ ከፍተኛውን ድጋፍ ያገኛሉ።