ዩኤስኤአይዲ ለምን ተቋቋመ? ትራምፕ እና መስክ ድርጅቱ እንዲዘጋ የሚፈልጉትስ ለምንድን ነው?
የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት በፈረንጆቹ 1961 የተመሰረተው በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሶቪየት ህብረት ተጽዕኖን ለመቀነስ ነበር
ድርጅቱ የእርዳታ አቅራቢ ተቋም ነው ወይስ የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ማስፈጸሚያ የሚለው ማከራከሩን ቀጥሏል
"አሜሪካ ትቅደም" በሚል መርሃቸው የሚታወቁት ፕሬዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደስልጣን እንደተመለሱ የውጭ እርዳታን ለ90 ቀናት እንዲቋረጥ አዘዋል።
በመላው አለም የሰብአዊ ድጋፍ የሚያቀርበውን የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በአሜሪካ መንግስት ስር ሆኖ እንደገና እንዲደራጅም ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ውሳኔው በአሜሪካ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ተቋማት እና በሚሊየኖች የሚቆጠሩ እርዳታ ፈላጊ ወገኖች አደጋ ላይ እንደሚጥል ተሰግቷል።
የትራምፕ አስተዳደር ግን ውሳኔው የአሜሪካ ግብር ከፋዮች ሀብትን ከብክነት ለመታደግ ግምገማ ለማካሄድ የሚያስችል መሆኑንና አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደማያካትት ይገልጻል።
"ዩኤስኤአይዲ" ምንድን ነው?
35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እንዲመሰረት አድርገዋል።
የቀዝቃዛው ጦርነት ውጥረት ከፍታ ላይ በደረሰበት በፈረንጆቹ 1961 የተቋቋመው የተራድኦ ድርጅት ሲመሰረት ዋነኛ አላማው በውጭ እርዳታ ስም የያኔዋን ሶቪየት ህብረት ተጽዕኖ መቀነስ እንደነበር አሶሼትድ ፕረስ ያወሳል።
የእርዳታ ድርጅቱን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ማድረግ ቢሮክራሲያዊ ችግር ይኖረዋል ብለው ያሰቡት ኬኔዲ ዩኤስኤአይዲ ከመንግስት ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም አድርገዋል።
የ64 አመት እድሜ ያለው አንጋፋ ተቋም ከሶቪየት መፈራረስ በኋላም የአሜሪካ አለማቀፍ ተጽዕኖ መፍጠሪያ መሳሪያ ሆኖ ቀጥሏል።
የዩኤስኤአይዲ ደጋፊዎች በድርጅቱ በኩል በመላው አለም የሚደረጉ ድጋፎች የሩሲያ እና ቻይናን ተጽዕኖ ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው ይላሉ። ቻይና በ"አንድ ቀበቶ አንድ መንገድ" ፕሮጀክት ለበርካታ ሀገራት ድጋፍ የምታደርገው በየዋህነት አይደለም፤ አሜሪካም በዩኤስኤአይዲ በኩል የውጭ ፍላጎቷን ለማስጠበቅ መስራቷ አያስወቅሳትም ሲሉ ይከራከራሉ።
አሜሪካውያን የተራድኦ ድርጅቱ ተቺዎች ደግሞ የሀገሪቱን ሀብት ያለአግባብ እንዲባክን አድርጓል፤ የሊብራሎችን አጀንዳ ያራምዳል ሲሉ ይወቅሱታል።
በበርካታ ሀገራት በድርጅቱ ድጋፍ ረሃባቸውን ያስታገሱ፤ የግብርና ስራቸው የተቃናላቸው እና ሌሎች እርዳታዎችን ያገኙ ዜጎች ደግሞ የአሜሪካውን ተቋም ሲያመሰግኑ ይደመጣል።
የውጭ እርዳታ "የአሜሪካ የብሄራዊ ደህነነት ሁነኛ ማስጠበቂያ ነው" - ሩቢዮ
የአለማቀፉ የልማት ተራድኦ ድርጅት ጉዳይ ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖችንም ለአመታት ሲያከራክር ቆይቷል። ሪፐብሊካኖች ድርጅቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ሆኖ ቁጥጥር ይደረግበበት ይላሉ። ዴሞክራቶች ደግሞ ገለልተኛ እና ነጻ እንዲሆን ይሻሉ።
ሪፐብሊካኖች ለመንግስታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎች፣ ለሰላም ማስከበር፣ ለሰብአዊ መብት እና የስደተኞች ጉዳይ ተቋማት የሚደረግ ድጋፍ እንዲቀንስ ፍላጎት አላቸው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ለበርካታ የመንግስታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎች የሚከፈል መዋጮን አቁርጠዋል። የተመድ የሰነህዝብ ፈንድ እና የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክርቤት ድጋፉ ከተቋረጠባቸው ውስጥ ናቸው።
ሁለቱ የአሜሪካ ፓርቲዎች ለውጭ የሚደረጉት ድጋፎች ግልጸኝነት እና መጠኑ ያከራክራቸው እንጂ ከናካቴው ይቅር ሲሉ አይደመጡም።
የፍሎሪዳው ሴነተር ማርኮ ሮቢዮ (የአሁኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር) በ2017 በማህበራዊ ሚዲያቸው በለጠፉት ጽሁፍ የውጭ እርዳታ "ልግስና አይደለም፤ የአሜሪካ የብሄራዊ ደህነነት ሁነኛ ማስጠበቂያ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
"ወንጀለኛ ድርጅት" - መስክ
የመንግስት ስራ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የሚሰራውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ("ዲኦጂኢ") እንዲመሩ በትራምፕ የተሾሙት የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ኤለን መስክ የመንግስት ወጪን የሚቀንሱ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እያደረጉ ነው።
የመንግስት ሰራተኞች ስራቸውን እንዲለቁ እና በትሪሊየን ዶላር የሚቆጠር የመንግስት ወጪን ለመቀነስ በትራምፕ የተላለፉ ውሳኔዎችን በማስፈጸም ላይ ናቸው።
የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅትም የኤለን መስክ ቀዳሚ ኢላማ ሆኗል። መስክ የዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ ገዳይ ፕሮግራሞችን ለማስፈጸም ውሏል በማለት ድርጅቱን "ወንጀለኛ" ብሎታል።
የተቋሙ ሰራተኞች በትናንትናው እለት በዋሽንግተን በሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤት እንዳይገቡ ተከልክለዋል። የድርጅቱ ድረገጽ እና የኤክስ ማህበራዊ ትስስር ገጽም አገልግሎት አቁመዋል።
በዩኤስአይዲ ስራ ማቆም ማን ክፉኛ ይጎዳል?
ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት በእርዳታ ድርጅቱ መዘጋት ከየትኛውም ክፍለአለም በበለጠ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል። አሜሪካ ባለፈው አመት በዚህ ቀጠና ለሚገኙ ሀገራት 6.5 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች።
በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግላቸውና የኤችአይቪ ቫይረስ ተጠቂዎችን የሚያስተናግዱ ክሊኒኮች በራቸውን መዝጋታቸውም በርካታ አፍሪካውያንን ለጉዳት ሊዳርግ እንደሚችል ተገልጿል።
በሜክሲኮ፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ኢኳዶር እና ጓቲማላ ወደ አሜሪካ በህጋዊ መንገድ ለመግባት የሚጠባበቁ ስደተኞች ማመልከቻ የሚያስገቡባቸው ቢሮዎች ተዘግተዋል።
አሜሪካ ለውጭ እርዳታ በየአመቱ ምን ያህል ታወጣለች?
የአለማችን ቀዳሚዋ የእርዳታ ለጋሽ ሀገር አሜሪካ በ2023 የ68 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን የሀገሪቱ መንግስት መረጃ ያሳያል። ይህም ከአመታዊ በጀቷ ከ1 በመቶ በታች ነው።
ኬዝር ፋሚሊ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ግን አብዛኞቹ አሜሪካውያን ሀገራቸው ከፌደራል በጀቷ 31 በመቶውን ለውጭ እርዳታ እንደምታውለው ያምናሉ ብሏል።
የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ በመጋቢት 2023 ያደረገው የዳሰሳ ጥናትም ከ10 ወጣቶች ሰባቱ አሜሪካ ለውጭ እርዳታ የምታውለው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ መሆኑንና በሀገር ውስጥ ለትምህርት፣ ጤና እና ማህበራዊ ዋስትና ከምትመድበው የላቀ መሆኑ እንደሚያምኑ አመላክቷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕም የአሜሪካውያን ግብር ከፋዮች ገንዘብ ያለአግባብ እየባከነ መሆኑን ደጋግመው መግለጻቸው አይዘነጋም።