የየመን አማጺያን ወደ እስራኤል የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃት መፈጸማቸው ተገለጸ
የአማጺያኑ ጥቃት በሜድትራኒያን ባህር ላይ ያለው የአሜሪካ ጦር አክሽፎታል ተብሏል
በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የድሮን ጥቃት በመፈጸም ላይ ይገኛል
የየመን አማጺያን ወደ እስራኤል የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃት መፈጸማቸው ተገለጸ፡፡
የእስራኤል ሀማስ/ፍልስጤም ጦርነት ከተጀመረ ሁለት ሳምንት የሖነው ሲሆን ጦርነቱ በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡
አሜሪካ ለእስራኤል የቀጥታ ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ በርካቶች ተቃውሟቸውን እየገለጹ ሲሆን እንደ ኢራን ያሉ ሀገራት እና በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ አማጺያን ደግሞ በግልጽ ዋሸንግተንን አስጠንቅቀዋል፡፡
የየመን ሁቲ አማጺያን አሜሪካ ከእስራኤል ጎን ከቆመች ሀማስን እንደሚያግዙ እና በእስራኤል ላይ ጥቃት እንደሚከፍቱ ባሳለፍነው ሳምንት አስጠንቅቀው ነበር፡፡
በዛሬው ዕለትም ከየመን ወደ እስራኤል ሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት ተተኩሷል የተባለ ሲሆን በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ያለው የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን ማክሸፉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ቀጠናዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቀች
አሜሪካ ለእስራኤል ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን እና ተተኳሾችን በመለገስ ላይ ስትሆን በሶሪያ እና ኢራቅ ባሉ ወታደራዊ ማዘዣዎቿ ላይ ጥቃት ተሰንዝሮባታል፡፡
አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ የጦር ሰፈሮቿ ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ስለመፈጸሙ ከመናገሯ ውጪ ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ በመላው ዓለም ያሉ አሜሪካዊያን ራሳቸውን ከጥቃት እንዲጠብቁ ያስጠነቀቀችው አሜሪካ ለእስራኤል ተጨማሪ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታውቃለች፡፡
በኢራን ድሮኖች በአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እና በእስራኤል ላይ ላይ ጥቃት ለመክፈት የሚደረገው ሙከራ ሊቀጥል እንደሚችል ስጋት መኖሩን የሀገሪቱ መከላከያ ገልጿል፡፡
አሜሪካ በራሷ እና በአጋሮቿ ላይ እየተፈጸሙባት ላሉ ጥቃቶች ምላሽ እንደምትሰጥም የገለጸች ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ሁለት የጦር አውሮፕላኖችን ከሁለት ሺህ የባህር ሀይል ወታደሮች ጋር ወደ መካከለኛው ምስራቅ መላኳ ይታወሳል፡፡