ኢትዮጵያ በካርቱም በሚገኘው ኤምባሲዋ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘች
በከባድ መሳሪያ የተፈጸመው ጥቃት ሰብአዊ ጉዳት ባያደርስም የአለም አቀፍ ህግና የቬይና ስምምነትን የጣሰ ነው ብሏል በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ
የኢትዮጵያ መንግስት ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ አጣርቶ ይፋ እንደሚያደርግም ነው ያስታወቀው
ኢትዮጵያ በሱዳን መዲና ካርቱም በሚገኘው ኤምባሲዋ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘች።
በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ኤምባሲው መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም በከባድ መሳሪያ ጥቃት እንደተፈጸመበት አረጋግጧል።
ጥቃቱ “ሰብዓዊ ጉዳት ባያደርስም የአለም አቀፍ ህግና የቬይና ስምምነትን የጣሰ በመሆኑ በጥብቅ እናወግዛለን”ም ነው ያለው።
ኤምባሲው በመግለጫው በከባድ መሳሪያ ተፈጽሟል ያለው ጥቃት በአየር ድብደባ ስለመፈጸሙም ሆነ ያደረሰውን ዝርዝር ጉዳት ከመጥቀስ ተቆጥቧል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በትናንትናው እለት በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ባጋረው መረጃ ግን በካርቱም ከተማ አል-አማራት አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ህንጻ በአውሮፕላን መደብደቡን መግለጹ ይታወሳል።
በሌ/ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር የአየር ኃይልም የአየር ድብደባውን ፈጽሙ የኤምባሲው ህንጻ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ነው አርኤስኤፍ ያስታወቀው።
የሱዳን ጦር እስካሁን ለዚህ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መግለጫ ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን፥ በሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው አልገለጸም።
“ጥቃቱ ከየትኛውም ወገን ቢሆን በፅኑ የሚወገዝ ነው” ያለው የኤምባሲው መግለጫ፥ መንግስት ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመና የጉዳቱን መጠን አጣርቶ ውጤቱን በቀጣይ እንደሚያሳውቅ አመላክቷል።
ሱዳን ከሚያዚያ ወር አጋማሽ ጀምሮ ግጭት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ በካርቱም የሚገኘው ኤምባሲ ከገዳሪፍ ሆኖ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል።
ኤምባሲው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማስቀጠልና በሱዳን ያለው ችግር ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚያደርገውንም ጥረት አጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት የደረሰውን ጥቃት በጽኑ እቃወማለሁ ብሏል።