የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት ከፍተኛ የሆነባቸው ሀገራት እነማን ናቸው?
ኢስዋትኒ፣ ሌሴቶ እና ደቡብ አፍሪካ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት ከፍተኛ የሆነባቸው ሀገራት ናቸው
የደቡብ አፍሪካ ሀገራት የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ከሆነባቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል ተጠቅሰዋል
የሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም በመጉዳት ለተለያዩ በሽታዎች በመዳረግ የሚታወቀው ኤችአይቪ ኤድስ አሁንም ፈዋሽ መድሃኒት አልተገኘለትም፡፡
በገዳይነቱ ከቀዳሚ የዓለማችን ቫይረሶች መካከል አንዱ የሆነው ኤችአይቪ ኤድስ በሌላው ዓለም ቀስ በቀስ የቀነሰ ቢሆንም በአፍሪካ ግን አሁንም ዋነኛ የሞት መንስኤ እንደሆነ ይገኛል፡፡
እንደ ዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ኢስዋትኒ ከአፍሪካ በኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት ቀዳሚዋ ሀገር ናት፡፡
ይህች ሀገር ካላት ጠቅላላ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 26 በመቶ ያህሉ በኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ተጠቅተዋል የተባለ ሲሆን ሌላኛዋ ደቡብ አፍሪካዊት ሀገር ሌሴቶ 19 በመቶ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ 17 በመቶ የኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት ያለባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
አልማዝ ማዕድን የበለጸገችው ቦትስዋና፣ ናሚቢያ እና ዚምባብዌም የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት ከፍተኛ የሆነባቸው የዓለማችን ሀገራት በሚል ተጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ አንድ ገዳይ በሽታ በተከሰተባቸው ሀገራት ያለው የስርጭት መጠን ከጠቅላላው ህዝብ ውስጥ አንድ በመቶ እና ከዛ በላይ ከሆነ ወረርሽኝ የሚል ስያሜ የሚሰጠው ሲሆን ይህን ወረርሽኝ ለመከላከል ልዩ ዘመቻ እንዲደረግ ይመከራል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት እንደ ሀገር ከ1 በመቶ በታች ቢሆንም በከተሞች ግን 3 በመቶ መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።