”ሰልፊ” የህብረተሰብ ጤና ችግር ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል - ጥናት
የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች ራስን በራስ ፎቶ በማንሳት (ሰልፊ) የ400 ሰዎች ህይወት ማለፉ ሪፖርት መደረጉን በጥናት አረጋግጠዋል
በአለማችን በየቀኑ በአማካይ 92 ሚሊየን “ሰልፊ” ፎቶዎች እንደሚነሱ ይገመታል
ራስን በራስ ፎቶ ማንሳት ወይንም ሰልፊ “የህብረተሰብ ጤና ችግር” ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው ተመራማሪዎች ገለጹ።
በአውስትራሊያ የኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ በ”ሰልፊ” ምክንያት የደረሰውን ሞት እና የአካል ጉዳት የተመለከተ ጥናት አድርገዋል።
በዚህም ከ400 በላይ ሰዎች ራሳቸውን ፎቶ ሲያነሱ ህይወታቸው ማለፉ ሪፖርት መደረጉን ነው ያመላከቱት።
አሃዙ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል በመጥቀስም የደቀነው አደጋ ከባድ መሆኑን አሳስበዋል።
አብዛኞቹ በ”ሰልፊ” ምክንያት ህይወታቸውን ያጡት ሴቶችና አማካይ እድሜያቸው 22 የሆኑ ወጣቶች መሆናቸውንም የጥናቱ መሪ ዶክተር ሳሙኤል ኮርኔል ይናገራሉ።
በአለማችን በስማርት ስልኮች በየቀኑ 92 ሚሊየን “ሰልፊዎች” እንደሚነሱ ይገመታል።
በ2013 በ”ሰልፊ” ምክንያት በሶስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሚያወሳው ጥናቱ ከስድስት አመት በኋላ (በ2019) ወደ 68 ማሻቀቡን አመላክቷል።
ህንድ ከፍተኛውን (100) የ”ሰልፊ” ሞትና ጉዳት በማስመዝገብ ቀዳሚ ናት። አሜሪካ በ39:፥ ሩሲያ ደግሞ በ33 ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።።
በአደገኛ ስፍራዎች ራስን በራስ ፎቶ ለማንሳት የሚደረጉ ጥረቶችና የሚጠፋውም የሰው ልጅ ህይወት እየጨመረ ቢሄድም ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ተመራማሪዎቹ ያምናሉ።
በ5 ጥናታዊ ጽሁፎች እና ከ12 በላይ የዜና ሽፋን ያገኙ የ”ሰልፊ” አደጋዎች ላይ ተመስርቶ የተከናወነው ጥናት ያሳየው ውጤት ጥልቅ ጥናት ቢደረግ ምን ያህል አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን ያመላክታል ብለዋል ዶክተር ሳሙኤል ኮርኔል።
በመሆኑም የማህበራዊ ትስስር ገጾች ራስን በራስ ፎቶ ማንሳት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ የተመለከቱ የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች ለተጠቃሚዎቻቸው እንዲያደርሱ ነው የጠየቁት።
ፎቶ ለመነሳት አደገኛ በሆኑ ስፍራዎች “ሰልፊ መነሳት ክልክል ነው” የሚሉና ሌሎች የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች እና ምልክቶች በስፋት መቀመጥ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።