የመኪና አደጋ የበርካቶችን ህይወት የሚቀጥፍባቸው ሀገራት
የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በመንገድ ላይ በሚከሰቱ አደጋዎች በየአመቱ ከ1 ነጥብ 19 ሚሊየን በላይ ሰዎች ህይወት ያልፋል
ጊኒ በተሽከርካሪዎች አደጋ በርካታ ሰዎች ከሚሞቱባቸው ሀገራት ቀዳሚዋ ሆናለች
በህንድ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ብቻ የ170 ሺህ ሰዎች ህይወት በተሽከርካሪ አደጋዎች ተቀጥፏል።
ይህም በየቀኑ 474 ሰዎች ወይንም በየሶስት ደቂቃው የአንድ ሰው ህይወት መንገድ ላይ ያልፋል እንደማለ ነው።
የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በመላው አለም በዚሁ አደጋ በየአመቱ 1 ነጥብ 19 ሚሊየን ሰዎች ህይወት ያልፋል ተብሎ ይገመታል።
የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በመኪና አደጋ የሚያልፈውን ህይወት በ2030 በግማሽ ለመቀነስ እቅድ ቢያስቀምጥም በአሜሪካ ብቻ በየእለቱ ከ19 ሺህ በላይ አደጋዎች ይከሰታሉ።
የመኪና አደጋ እድሜያቸው ከ5 እስከ 29 የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ቀዳሚው የሞት መንስኤ ነው።
በመንገድ ላይ እንደወጡ ከሚያስቀሩ አደጋዎች 90 በመቶው በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት መከሰታቸውም ከመንገድ ጥራት ጋር የተያያዘው ችግር ለአደጋው ቀዳሚ መንስኤ ሆኖ እንዲታይ አድርጓል።
የአለም ጤና ድርጅት በ197 ሀገራት የመረጃ ቋት በመመስረት ባደረገው ጥናት የምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ጊኒ በመኪና አደጋ በርካታ ዜጎችን በማጣት ቀዳሚዋ ሆናለች።
በጊኒ በ2021 ከ100 ሺህ ሰዎች ውስጥ የ37 ሰዎች ህይወት በተሽከርካሪ አደጋ አልፏል።
ከ100 ሺህ ሰዎች በርካታ ሰዎችን በአደጋው በማጣት ከፊት ከሚገኙት 20 ሀገራት 12ቱ በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው።