በርካታ ስደተኞችን የሚያስተናግዱ ሀገራት
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ከአጠቃላይ ህዝቧ 88 በመቶው ስደተኛ ነው

ከ50 ሚሊየን በላይ ስደተኞች የምታስተናግደው አሜሪካ በአለም ቀዳሚዋ ናት
ስደት የሰው ልጅ በካርታ እና ድንበር ሳይገደብ ጀምሮ ያለ የተሻለ ነገርን ፈለጋ አለያም መጥፎ ሁኔታን ሽሽት ለዘመናት ሲከናወን የቆየ ነው፡፡
ጦርነት ፣ ግጭት ፣ የፖለቲካዊ አለመረጋጋትን በመሳሰሉ በአስገዳጅ ምክንያቶች እና የተሻሉ አማራጮችን ለመቃኘት ሰዎች ከሀገር ሀገር በመንቀሳቀስ ኑሯቸውን ለማስቀጠል ይጥራሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገሮችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ገጽታ በመቅረጽ ረገድ ስደት ወሳኝ ሚና ስለመጫወቱ ይነገራል፡፡
ለሥራ፣ ለንግድ እና የተሻለ የኑሮ ጥራት እድሎችን በመስጠት ለስደተኞች ዓለም አቀፋዊ መናኸሪያ የሆኑ ሀገራት አሉ፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ እና ምዕራባውያን ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች ዋነኛ የስደተኞች መዳረሻ እና በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎችን በማስተናገድ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው።
አንዳንድ ሀገራት በሥራ ዕድል ምክንያት ስደተኞችን ሲስቡ ሌሎች ደግሞ በጠንካራ ማህበራዊ ስርዓቶች እና ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ በማቅረብ በስደተኞች ዘንድ ተመራጭ ይሆናሉ፡፡
የስደተኛ ፖሊሲዎች በየጊዜው እየተቀያየሩ በሚገኙበት በዚህ ወቅት የወደፊቱን ዓለም አቀፋዊ ስነ-ሕዝብ የሚቀርሱ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ፍልሰቶች በመላው አለም እየተካሄዱ እንደሚገኙ የወርልድ ፖፕሌሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ከህዝብ ቁጥራቸው አንጻር በርካታ ስደተኞችን በሚያስተናግዱ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡
ከአጠቃላይ ህዝቧ 88 በመቶ ስደተኛ በሆነባት ሀገር 8.7 ሚሊየን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የሚገኝው ኢኮኖሚ ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እና ከታክስ ነጻ ፖሊስን መከተሏ በብዙ ስራ ፈላጊ ስደተኞች ዘንድ ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
የአለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት አሜሪካ 50 ሚሊየን ስደተኞችን በማስተናገድ ከአለም ቀዳሚ ብትሆንም ከአጠቃላይ ህዝቧ አንጻር የስደተኞች ድርሻ 14 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ዋሽንግተን ለትምህርት ፣ ለስራ እና ለተሻለ ኑሮ ፈላጊ የአለም ህዝቦች አሁንም ቀዳሚ ተመራጭ በመሆን ቀጥላለች፡፡
ኩዌት፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ኦማን በደረጃ ሰንጠረዡ ከህዝባቸው ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ስደተኞችን በመያዝ የሚጠቀሱ ናቸው።
አውሮፓዊቷ ሀገር ሉክሰምበርግ በቆዳ ስፋቷ ትንሽ ብትሆንም በኢኮኖሚ ጠንካራ በመሆኗ ከአጠቃላይ ህዝቧ 48 በመቶ ስደተኛ ህዝብ ያላት ሀገር ነች፡፡