ሜክሲኮ ከአሜሪካ ህገ ወጥ ስደተኞችን ጭነው የሚመጡ አውሮፕላኖች እንዳያርፉ ከለከለች
በትላንትናው ዕለት ሲ-17 የተባለው የጦር አውሮፕላን ከአሜሪካ ከመነሳቱ በፊት ፈቃድ ተከልክሏል
በዕለቱ ሁለት ተመሳሳይ አውሮፕላኖች ከ80 በላይ ስደተኞችን አሳፍረው ወደ ጓቲማላ አቅንተዋል
ሜክሲኮ ስደተኞችን ያሳፈረ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን በግዛቷ እንዳያርፍ ከልክላለች፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ሰኞ ዕለት ስራ ከጀመሩ በኋላ በደቡባዊ ድንበር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ህገወጥ ስደተኞችን ከሀገር የማስወጣት ሂደትን እንደሚያጠናክሩ ቃል ገብተዋል።
ኤንቢሲ ኒውስ ሁለት የአሜሪካ የመከላከያ ባለስልጣናትን ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው ሲ-17 ወታደራዊ አውሮፕላን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ስደተኞችን አሳፍሮ ሜክሲኮ ለማረፍ እቅድ ይዞ የነበር ቢሆንም ሜክሲኮ አውሮፕላኑን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኗ ሳይነሳ ቀርቷል፡፡
አንድ የሜክሲኮ ባለስልጣን ለሮይተርስ የአሜሪካው አውሮፕላን በሜክሲኮ ለማረፍ ፍቃድ መከልከሉን ቢያረጋግጡም ሀገሪቱን ይህን ያደረገችበትን ምክንያት አላሳወቁም፡፡
የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ “ሜክሲኮ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ጥሩ ግንኙነት አላት፤ ስደትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሉዓላዊነታችንን ባከበረ መልኩ እንተባበራለን፤ ሜክሲካውያን ወደ ሀገራቸው ሲመጡ ሁል ጊዜ በደስታ እንቀበላቸዋለን” ብሏል።
ኤንቢሲ ኒውስ በምንጭነት የጠቀሳቸው የአሜሪካ ባለስልጣን ጉዳዩ ከአስተዳደራዊ ጉዳይ ጋር እንደሚያያዝ ተናግረው በቅርቡ ችግሩ እንደሚቀረፍ ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የኋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መረጃ ደግሞ ሜክሲኮ በአንድ ቀን 4 በረራዎችን ለመቀበል ተስማምታለች ብለዋል፡፡
በትላንትናው ዕለት ሁለት ተመሳሳይ በረራዎች 80 የሚጠጉ ስደተኞችን በመያዝ ወደ ጓቲማላ አቅንተዋል፡፡
በትራምፕ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፔንታጎን ተጨማሪ 1500 ወታደሮችን ቀደም ብሎ የላከ ሲሆን ከዚህ ባለፈም ቁጥራቸው 10 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮችን ወደ ድንበር ለመላክ እቅድ እያዘጋጀ ይገኛል፡፡
በድንበር ላይ የሚሰማሩት ወታደሮች ድንበሮችን የመጠበቅ፣ የድንበር መከለያዎች ግንባታ እና የስደተኞች ማቆያዎችን መጠበቅ ላይ እንደሚሰሩ ተዘግቧል፡፡
አዲሱ አስተዳደር በካሊፎርኒያ እና ቴክሳስ ግዛቶች ድንበር አቅራቢያ የሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች ስደተኞችን በጊዜያዊነት ለማቆየት እንዲዘጋጁ ትዕዛዝ መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡