ከአሜሪካ የተባረሩ ስደተኞችን እስካሁን ምን ያህል ሀገራት ተቀብለዋል?
ህገወጥ ስደተኞችን የጫነ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን ኩባ ጓንታናሞ ቤይ ደርሷል
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጓንታናሞ 30 ሺህ ህገወጥ ስደተኞችን ለማስፈር አቅደዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ህገወጥ ስደተኞችን ከሀገሪቱ የማስወጣት እርምጃቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
ትናንት ምሽትም የተባረሩ ስደተኞችን የጫነ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን ኩባ መግባቱን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባህር ሃይል ጣቢያ በሚገኝበት ጓንታናሞ ቤይ 30 ሺህ ስደተኞችን ለማስፈር ያቀዱ ሲሆን፥ ስደተኞቹን የሚያስተናግድ ሰፊ ማዕከል እንዲገነባም ማዘዛቸው ይታወሳል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ፔት ሄስጌት ጓንታናሞ ቤይ ስደተኞችን ለማስፈር "ትክክለኛው ቦታ" ነው ብለዋል። ባለፉት ቀናትም ተጨማሪ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ስፍራው በማቅናት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ነው ያነሱት።
ኩባ እና አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ግን ስደተኞችን በጓንታናሞ የማስፈር እንቅስቃሴን አጥብቀው ተቃውመውታል።
የኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉየል ዲያዝ ካነል፥ "የአሜሪካ መንግስት በህገወጥ መንገድ በተያዘው የኩባ ግዛት፣ በጓንታናሞ ባህር ሃይል ጣቢያ ስደተኞችን ለማሰር መወሰኑ እጅግ አረመኔነት ነው" ብለዋል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የስደተኞች መብት ፕሮግራም ዳይሬክተር አሚ ፊሸርም ስደተኞችን ከጠበቆች፣ ቤተሰቦችና ደጋፊዎቻቸው የሚለያይ ነው ያሉት "አሰቃቂ" ድርጊት እንዲቆም ጠይቀዋል።
ከመስከረም 11ዱ ጥቃት ማግስት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ "በሽብርተኝነት ላይ ባወጁት ጦርነት" የተከፈተው የጓንታናሞ እስርቤት የአልቃይዳ አባላትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ታጉረውበታል።
ከእስር ቤቱ ጎን ይከፈታል የተባለው የስደተኞች ማቆያም 30 ሺህ ሰዎችን እንዲይዝ ዝግጅቱን እንዲመሩ የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄስጌት በትራምፕ ተሹመዋል።
የተባረሩ ስደተኞችን የተቀበሉ ሀገራት
እስካሁን ወደ ኢኳዶር፣ ሆንዱራስ፣ ፔሩ እና ጉዋም በሰባት በረራዎች ስደተኞች ከአሜሪካ እንዲወጡ ተደርጓል።
ኮሎምቢያ በራሷ አውሮፕላን በሁለት በረራዎች የተባረሩ ዜጎቿን አስወጥታለች።
ጓቲማላ በሁለት በረራዎች 160 ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቿን መቀበሏም የሚታወስ ነው።
አሜሪካ ከትናንት በስቲያም ህንዳውያን ህገወጥ ሰደተኞችን ወደ ሀገራቸው መመለሷ ተዘግቧል። ከ750 ሺህ በላይ በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የገቡ ህንዳውያን በትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ወደመጡበት የመመለስ ስጋት ተደቅኖባቸዋል።
የአሜሪካ ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ማስፈጸሚያ (አይሲኢ) ከህዳር 2024 ጀምሮ ከሀገር የሚያስወጣቸውን ከ1 ሚሊየን 445 ሺህ በላይ ህገ ወጥ ስደተኞች የመጨረሻ ዝርዝር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ከዚህ ውስጥ 41 ሺህ 323 ህገወጥ አፍሪካውያን ስደተኞች የተካተቱ ሲሆን ሶማሊያ በርካታ ዜጎቿ የሚባረሩባት ሀገር ናት።