በርካታ ቋንቋ የሚነገርባቸው የአለም ሀገራት
በአለም አቀፍ ደረጃ ከ7ሺህ በላይ ቋንቋዎች እንደሚነገሩ መረጃዎች ያመላክታሉ
እስያ እና አፍሪካ በርካታ ቋንቋዎች ከሚነገርባቸው የአለም ክፍሎች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው
በሰው ልጅ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ባህላዊ እና አጠቃላይ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ ቋንቋዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ይነገራል፡፡
በቋንቋ እና በስራ ቋንቋ መካከል ልዩነት ቢኖርም አንዳንድ ሀገሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።
የስራ ቋንቋዎች ለመንግስት አገልግሎት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ብሔራዊ ሚዲያዎች እና ለመሳሰሉት ያገለግላሉ።
እንደ ጃፓን ያሉ አንዳንድ ሀገራት በአንድ የስራ ቋንቋ (ጃፓንኛ) ብቻ ይጠቀማሉ ፤ ህንድ በተወሰኑ የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ 23 የስራ ቋንቋዎችን ተግባራዊ ስታደርግ በመላ ሀገሪቱ 16 ሥራ ቋንቋዎችን የምትገለገለው ዚምባቡዌ ከአለም ቀዳሚዋ ነች፡፡
በቋንቋዎች ላይ ጥናት እና ምርምር የሚሰራው የ“ኢትኖሎግ” መረጃ እንደሚያመላክተው በአለም አቀፍ ደረጃ 7151 ቋንቋዎች ይነገራሉ፡፡
2300 ቋንቋዎች የሚነገሩበት እስያ አህጉር በደረጃው ቀዳሚ ሲሆን አፍሪካ በ2144 ፣ የፓስፊክ ቀጠና በ1313 ቋንቋዎች ይከተላሉ፡፡
ከአውሮፓ አህጉር በሁለት እጥፍ 840 ቋንቋ የሚነገርባት ደሴታማዋ ሀገር ፓፑዋ ኒው ጊኒ በዓለም ላይ ከፍተኛ የቋንቋ ብዝሃ የሚገኝባት ሀገር ናት፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ ሁለተኛዋ ኢንዶኔዥያ ስትሆን በመላ ሀገሪቱ 712 የተለያዩ ቋንቋዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፤ የ522 ቋንቋዎች ባለቤት የሆነችው ናይጄሪያ ደግሞ ሶስተኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በአለም ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎች እንዳሉ ቢገለጽም ከአጠቃላይ 40 በመቶ የሚሆኑት የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው፡፡