የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና አይስላድ ከዓለማችን ሰላማዊ አገራት ቀዳሚ ናቸው ተባለ
በ2020 የ“ግሎባል ፋይናንስ” ሪፖርት ከ163 የዓለማችን አገራት 139ኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ ደረጃዋን አሻሽላ 83ኛ ሆናለች
ፊሊፒንስ እና ናይጀሪያ ደግሞ ሰላም የራቃቸው የዓለማችን አገራት መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል
“ግሎባል ፋይናንስ” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም የፈረንጆች 2021 ዓመት የዓለማችንን አገራት ደህንነት ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
በተቋሙ ዓመታዊ ሪፖርት መሰረት አይስላንድ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና ኳታር ከዓለማችን 134 አገራት አስተማማኝ ደህንነት ያለባቸው ቀዳሚዎቹ አገራት ናቸው።
ተቋሙ የአገራቱን ደህንነት ለመመዘን ከተጠቀመባቸው መስፈርቶች መካከል በአገራቱ ያሉ ግጭቶች፣ የኮሮና ቫይረስ ጉዳት፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሽብር ቡድኖች ጥቃት የመጋለጥ እድል፣ ዓመታዊ የወታደራዊ በጀት እና የቤት ውስጥ ጥቃቶች መጠን ዋነኞቹ ናቸው።
በነዚህ መስፈርቶች መሰረት አይስላንድ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ኳታር፣ ሲንጋፖር እና ፊንላንድ በአንጻራዊነት ደህንነታቸው የተረጋገጠባቸው አገራት መሆናቸው ተገልጿል።
ፊሊፒንስ፣ ኮሎምቢያ፣ ጓቲማላ፣ ናይጀሪያ እንዲሁም ቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና በዓለማችን ደህንነታቸው ያልተረጋገጠባቸው አገራት መሆናቸውን ተቋሙ ገልጿል።
ግሎባል ፋይናንስ ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ኒዮርክ ያደረገ ዓለም አቀፍ የግል ተቋም ሲሆን ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ ጥናቶችን በማካሄድ ለአገራት እና የቢዝነስ ተቋማት የውሳኔ ግብዓት የሚሆኑ ሪፖርቶችን የሚያወጣ ተቋም ነው።
ከአፍሪካ ሞሮኮ፣ሞሪሺየስ እና ቦትስዋና በአንጻራዊነት የተሻለ ደህንነት ያለባቸው አገራት እንደሆኑ ሪፖርቱ ያስረዳል።
በ2020 የ“ግሎባል ፋይናንስ” ሪፖርት ከ163 የዓለማችን አገራት 139ኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ ዘንድሮ ደረጃዋን አሻሽላ 83ኛ ሆናለች፡፡
ድርጅቱ በዚህ ዓመት በኮሮና ቫይረስ እና በሌሎች ምክንያቶች በሪፖርቱ ያካተታቸው አገራት ዝርዝር ወደ 134 ዝቅ ማለቱንም አስታውቋል።