በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ በሁለት ዓመት ውስጥ ሰባተኛው መፈንቅለ መንግስት በጋቦን ተፈጽሟል
የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ መፈንቅለ መንግስት እንዳሳሰበው ገለጸ።
ከሁለት ወር በፊት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር መፈንቅለ መንግስት ተጽሞ የሐገሪቱ ጦር ስልጣን በሀይል መቆጣጠሩ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ በሌላኛዋ የነዳጅ እና ማግኒዢየም ምድር በመባል የምትታወቀው ጋቦን ተመሳሳይ ክስተት መፈጸሙ ተገልጿል፡፡
ጋቦን ላለፉት 56 ዓመታት ቦንጎ ቤተሰብ ስር ስትተዳደር የቆየች ሲሆን ባሳለፍነው ቅዳሜ በተካሄደ ምርጫ ማሸነፋቸውን ያወጁት ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን መነሳታቸውን የሀገሪቱ ጦር አባላት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮችና ደህንነት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል በአፍሪካ እየተፈጸሙ ያሉ የመንግስት ግልበጣውፕች አሳሳቢ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ቦሬል አክለውም አውሮፓ ህብረት በስደተኞች፣ ሽብርተኝነት እና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር እየሰራ በመንግስታት ላይ የሚፈጸሙ መፈንቅለ መንግስቶች ፈተና ሆነውብናል ብለዋል።
ከዚህ በፊት በቻድ፣ ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ፣ ሱዳን፣ ኒጀር እና ሁን ደግሞ በጋቦን መፈጸሙ አሳሳቢ መሀኑን የተናገሩት ጆሴፍ ቦሬል በሃይል የሚደረግ የመንግስት ለውጡ በተለይም በምዕራብ አፍሪካ በተደጋጋሚ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በምዕራብ አፍሪካ እየተፈጸሙ ባሉ መፈንቅለ መንግስታት እና ጉዳታቸው ዙሪያ እንደሚመክሩም ተገልጿል፡፡
ጋቦን ከአፍሪካ በነዳጅ ሀብቷ አምስተኛዋ ሀገር ስትሆን ማግኒዢየም እና ሌ ሎች ሀብቷም የሀብት ምድር በመባል ትታወቃለች።
የፈረንሳይም ቅኝ ግዛት የነበረች ሲሆን የአሁኑ መፈንቅለ መንግስት ለፓሪስ ተጨማሪ ራስ ምታት ሆኗል ተብሏል።
ከስምንት ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት የፈረንሳይ የማዕድን አውጪ ኩባንያ ኢራሜት ለደህንነት ሲል ለጊዜው ስራውን እንዳቆመ አስታውቋል፡፡
ፈረንሳይ በሊቨርቢል የተፈጸመውን መፈንቅለ በጥብቅ መንግስት እየተከታተለች መሆኗን የገለጸች ሲሆን በኒጀር የተፈጠረውን ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግስት መፍትሄ ለማበጀት ከኢኮዋስ እና ሌሎች ሀገራት ጋር በመምከር ላይ እንደነበረች ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
የጋቦን ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ታሰረዋል የተባለ ሲሆን የሀገሪቱ መውጫ እና መግቢያ ድንበሮች ለጊዜው ተዘግተዋል ተብሏል፡፡