ፖለቲካ
የአውሮፓ ህብረት የዩክሬን ስንዴ ወደ አምስት የህብረቱ ሀገራት እንዳይገባ አገደ
ህብረቱ ውሳኔውን ያሳለፈው የአውሮፓ ገበሬዎችን አመጽ ተከትሎ ነው ተብሏል
ፖላንድ፣ ሮማኒያ፣ ሀንጋሪ፣ ስሎቬኒያ እና ቡልጋሪያ የዩክሬን ምርቶች እንዳይገቡባቸው የተደረጉ ሀገራት ናቸው
የአውሮፓ ህብረት የዩክሬን ስንዴ ወደ አምስት የህብረቱ ሀገራት እንዳይገባ አገደ።
የአውሮፓ ህብረት የዩክሬን ስንዴ እና ሌሎች የጥራጥሬ ምርቶች ፖላንድን ጨምሮ ወደ አምስት ሀገራት እንዳይገባ እገዳ ጥሏል።
የዩክሬን ስንዴ እና ሌሎች ጥራጥሬ ምርቶች በርካሽ ዋጋ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መግባቱን ተከትሎ ነበር ተቃውሞ የተሰማበት።
በተለይም የፖላንድ፣ ሮማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ሀንጋሪ እና ስሎቬኪያ ገበሬዎች ከዩክሬን ስንዴ ምክንያት የምርቶቻቸው ዋጋ ቀንሶብናል በሚል በተቃውሞ ላይ ነበሩ።
የአውሮፓ ህብረትም ከገበሬዎቹ የቀረበውን ተቃውሞ ምክንያት በማድረግ የዩክሬን ስንዴ እና ሌሎች የጥራጥሬ ምርቶች እንዳይገቡ እገዳ አስተላልፏል ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት እገዳም እስከ ቀጣዩ መስከረም ወር ድረስ ይቆያል የተባለ ሲሆን ኪቭ ምርቶቿን ተቃውሞ በተነሳባቸው አምስት ሀገራት ላይ ከማጓጓዝ ውጪ መሸጥ አትችልም ተብሏል።
ዩክሬን እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ያልሰጠች ሲሆን በተመድ እና ቱርክ አደራዳሪነት የግብርና ምርቶቿን በጥቁር ባህር በኩል ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች።