የጊኒ እና ጋቦን መፈንቅለ መንግስታት ብዙ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን እንቅልፍ ነስቷል ተብሏል
በአፍሪካ የመፈንቅለ መንግሥት ስጋት ያለባቸው ሀገራት እነማን ናቸው?
በአፍሪካ በተለይም የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ሀገራት በተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግስት እየተፈጸመባቸው ይገኛል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ ስምንት መፈንቅለ መንግስት ተሞክረው ሰባቱ ስልጣን በሀይል ተቆጣጥረዋል።
በያዝነው የክረምት ወቅት ብቻ በኒጀር እና ጋቦን በተፈጸመ መፈንቅለ መንግስት የሀገራቱ ወታደሮች ስልጣን በሀይል ተቆጣጥረዋል።
ይህን ተከትሎም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ይህ ነገር ወደ እኛም ሊመጣ ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ፋይናንሺያል ታየምስ ዘግቧል።
የፖለቲካ ተንታኞችን ዋቢ አድርጎ የተሰራው ይህ ዘገባ ስልጣን በወታደራዊ ሀይሉ እንቀማለን በሚል ስጋት የገባቸው ሀገራትም የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው ተብሏል።
ወታደራዊ አመራሮች ላይ ሽግሽግ ማድረግ፣ ለጦር መሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ መክፈል እና ሌሎች ማባበያዎችን መስጠት በስልጣን ላይ ያሉ የአፍሪካ መሪዎች ድርጊት እንደሆነ ተገልጿል።
የካሜሩኑ ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ፣ የየሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ ንጉዌሶ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒው ቲዮዶር ኦቢያንግ፣ የቶጎው ፕሬዝዳንት ፋውሬ ግናሲንግቤ ከፍተኛ የመፈንቅለ መንግሥት ስጋት ያጠላባቸው ሀገራት ናቸው ተብሏል።
ከሁለት ዓመት በፊት አባታቸውን ተክተው ወደ ስልጣን የመጡት መሀማት እድሪስ ዴቤ መፈንቅለ መንግሥት ሊፈጸምባቸው ይችላሉ የሚል ስጋት ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዱ ሲሆኑ ሴኔጋል እና ኮትዲቯር ደግሞ በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የመፈንቅለ መንግሥት ግምት የተሰጣቸው ሀገራት እንደሆኑ ተገልጿል።
ዋና መቀመጫውን ለንደን ባደረገው ቻታም ሀውስ የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ፖል ሜሊ እንዳሉት ለመፈንቅለ መንግሥት ስጋት የተዳረጉ ሀገራት በጥድፊያ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው ብለዋል።
ስጋት የገባቸው መሪዎች ሀብታቸውን ወደ ሚተማመኑባቸው አካላት እያዛወሩ ነው የሚሉት ተንታኙ ታማኝ የጦር ጀነራሎችን እየለዩ እና እየሾሙ እንደሆነም ተናግረዋል።
እንደ ካሜሩኑ ፕሬዝዳንት አይነት ረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ የቆዩ ኔሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም ስልጣናቸውን ለልጃቸው አልያም ለሚያምኑት ሰው ስለሚያስረክቡበት በማሰብ ላይ እንደሆኑም ሌሎች የአፍሪካ ጉዳዮች ምሁራን ጠቅሰዋል።