የኒጀር መፈንቅለ መንግስት አቀነባባሪ ጀነራል አብዱራህማን ማን ናቸው?
ጀነራሉ መፈንቅለ መንግሥቱን የፈጸሙት ኒጀራዊያንን ለመታደግ ሲሉ እንደሆነ ተናግረዋል
የ62 ዓመቱ ጀነራል ላለፉት 12 ዓመታት የፕሬዝዳንት ጋርድ ዋና አዛዥ ነበሩ
በቅጽል ስሟ የዩራኒየም ምድር በመባል እምትታወቀው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር ከሰሞኑ መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሞባታል።
የፕሬዝዳንቱ ጠባቂዎች ፕሬዝዳንት መሀመድ ባዙም በቤተ መንግስታቸው እንዳሉ እንዳይንቀሳቀሱ ታግተዋል።
ጠባቂዎቹ ከእገታው በኋላ በፕሬዝዳንት ባዙም የሚመራው መንግሥት መፍረሱን እና ጀነራል ቲያኒ የሀገሪቱ ሙሪ መሆናቸውን በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
የዚህ መፈንቅለ መንግሥት ዋነኛ አቀነባባሪ ጀነራል አብዱራህማን ቲያኒ መሆናቸውም ታውቋል።
ይህን ተከትሎም ጀነራል ቲያኒ ማን ናቸው? እሚለው የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ጀነራል አብዱራህማን በኒጀር እና ማሊ አዋሳኝ ድንበር ካለች ቲላቤሪ ከተሰኘ ክልል የተወለዱ ሲሆን በሀገሪቱ አሉ የሚባሉ ወታደራዊ አዛዥ ናቸው።
የ62 ዓመቱ ጀነራል ላለፉት 12 ዓመታት የፕሬዝዳንታዊ ጋርድ ዋና አዛዥም ሆነው እንደሰሩ ሮይተርስ ዘግቧል።
በጀርመን የኒጀር ኢምባሲ ውስጥ ለረክም ዓመታት ወታደራዊ አታቼ ሆነው አገልግለዋል የተባሉት እኝህ የጦር መሪ ልታይ ልታይ የማይሉ ነበሩም ተብላል።
በሳህል ቀጠና ኒጀር ያደረገቻቸውን ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች መርተዋል የተባሉት ጀነራል አብዱሮህማን በተለይም ህገወጥ ንግድን እና ሽብርተኝነት ለመከላከል የተካሄዱ ስምሪቶችን በመምራትም ይታወቃሉ።
ጀነራሉ ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ "የቴክኒክ እና ፋይናንስ አጋሮቻችን የገጠመንን ፈተና በድል እንድንዉጣ ድጋፍ አድርጉልን" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጀነራሉ የምዕራባዊያን ዋነኛ አጋር የሚባሉት ፕሬዝዳንት ባዙምን ከስልጣን በሀይል ማስወገዳቸውን ተከትሎ ውግዘት የገጠማቸው ሲሆን የአውሮፓ ህብረት ለሀገሪቱ ይሰጠው የነበረውን ድጋፍ ማቋረጡን አስታውቋል።
ከዓለም ዩራኒየም ሀብት ውስጥ የሰባት በመቶ ድርሻ ያላት ኒጀር የአሜሪካን እና ፈረንሳይ ወታደሮችን በሀገሯ አስፍራለች።