የጦር መሪው "ህገ መንገስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል" ተጠርጥረው ነው የታሰሩት
በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ተወሰነ፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ባስቻለው ችሎት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ መወሰኑን ባለቤታቸው ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል፡፡
ወ/ሮ መነን ኃይሌ ብርጋዴል ጄኔራል ተፈራ ማሞ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅና ከእስር እንዲወጡ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግንቦት ወር ላይ ባስቻለው ችሎት በጄ/ል ተፈራ ማሞ ላይ የ10 ቀን ጊዜ ቀጠሮ መፍቀዱ ይታወሳል፡፡ የጦር መኮንኑ "ህገ መንገስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል" በሚል ተጠርጥረው መታሰራቸውና ፍርድ ቤት መቅረባቸው የሚታወስ ነው፡፡
ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ በአዲስ አበባ ከተማ "ባልታወቁ ሰዎች ታፍነው" ያሉበት ሳይታወቅ ቀናት ከተቆጠሩ በኋላ ነው ባህር ዳር እንደሚገኙ የተገለጸው፡፡
ብርጋዴር ጄኔራሉ ለመጨረሻ ጊዜ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ በመሆን የተሾሙት ባሳለፍነው ዓመት ወርሃ ሃምሌ ላይ ነበር፡፡ ከሹመት በኋላም የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር ባደረገው ጦርነት በፌደራል መንግስት ጦር እዝ ስር በመሆን ውጊያ ሲመሩ፣ ሲዋጉና ሲያዋጉ መቆየታቸው ይታወሳል።