አባ ሳዊሮስን ጨምሮ 29 ግለሰቦች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር እንዳይገቡ በፍ/ቤት ታገዱ
ፍርድ ቤቱ ቤተክርስቲያኗ ያቀረበችውን አቤቱታ ተከትሎ ነው እግድ የጣለባቸው

ፌደራል ፖሊስ ህግ እንዲያስከብር እና ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ እንዳይገቡ ፍርድ ቤት መወሰኑ ተገልጿል
ፍርድ ቤቱ፤ ቤተክርስቲያኗ በቀኖና እና ስርአተ ቤተክርስቲያን ጥሰት ምክንያት ያወገዘቻቸውን የኃይማኖት አባቶች ጨምሮ በ29 ግለሰቦች ላይ ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ እግድ አስተላልፏል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በቀድሞ መጠሪያቸው አባ ሳዊሮስ በሚል በሚጠሩት አማካኝነት የሚመራ ቡድን "አዲስ ሲኖዶስ" አቋቁመናል መባሉን ተከትሎ ችግር መፈጠሩ ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗ በራሷ ስርዓት እርምጃ የወሰደች ሲሆን ንብረቶቿን ደግሞ ይህ ቡድን እንዳይጠቀም መንግሥት ህግ እንዲያስከብር ጠይቃም ነበር።
ይሁንና መንግሥት ህግ ባለማስከበሩ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗ የህግ ቡድን በማቋቋም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዷን አስታውቃለች።
ይህ የቤተ ክርስቲያኗ የህግ ቡድን በዛሬው ዕለት በፍርድ ቤት እግድ እንዲተላለፍለት ያቀረበው አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠቱን ገልጿል።
የቀድሞ የቤተ ክርስቲያኗ ጳጳሳት እንዲሁም 25 አዲስ የተሾሙ ጳጳሳት በአጠቃላይ 29 ግለሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ ፍርድ በቤት እግድ አውጥቷል ሲል የቤተክርስቲያኗ የህግ ቡድን እና ጠበቆች ተናግረዋል ።
ከዚህ በተጨማሪም የፌደራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ፖሊስም የቤተክርስቲያት ቅጽር ግቢ ውስጥ እንዳይገቡ እና ህግ እንዲያስከብር ፍርድ ቤት ትእዛዝ ተሰጥቷልም ተብሏል።
ይህን የፍርድ ቤት እግዱ ጥሶ የገባ ማንኛውም አካል በወንጀል እንደሚጠየቅም ይህ የቤተ ክርስቲያኗን ጥቅም ለማስከበር የተቋቋመው የህግ ቡድን አስታውቋል።
የህግ ቡድን አባላቱ አክለውም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ሂደት አቁሙ እስከሚለን ድርስ የህግ ሂደቱን እንቀጥላለንም ብለዋል።
የጸጥታ አካላት የተላለፈውን እግድ እንዲያስፈጽሙ እንዲሁም የሰላም ሚኒስቴርም ሂደቱን እንዲከታተል ፍርድ ቤት ትእዛዝ መስጠቱ ተገልጿል።
በተያያዘ ዜና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኗ ቅሬታዎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር በቤተ መንግሥት እንደተወያዩ ተናግረዋል ።
ቤተ ክርስቲያኗ በመንግስት ላይ ያቀረበችውን አቤቱታ ጠቅላይ ሚንስትሩ መረዳታቸውን ያስታወቀው ቅዱስ ሲኖዶስ የውይይቱ ዝርዝር ይዘት እና ቀጣይ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ነገ መግለጫ እንደሚሰጥም ቤተ ክርስቲያኗ አስታውቃለች።