ቤተክርስቲያኗ የጠራችው ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይ ይካሄዳል - ቅዱስ ሲኖዶስ
መንግስት ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቋል
መንግስት ባወጣው መግለጫ ግን የተጠራው ሰልፍ እንዳይደረግ መከልከሉና ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን መግለጹ ይታወሳል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠራችው ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ስልፍ “ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ” እንደሚካሄድ ገለጸች።
መንግስት “ከሕገወጦቹ ግለሰቦች ጋር በመተባበር በአደባባይ እየፈጸመ ያለውን የሕግ ጥሰት በሁለት ቀናት ውስጥ እንዲያቆም”ም ነው ቅድሱ ሲኖዶስ የጠየቀው።
መንግሥት ሕግ እየጣሰ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ግን ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የጣሰውን ሕግ መሠረት በማድረግ መብቷን ለማስከበር እንደምትገደድ ነው የተጠቆመው።
- መንግስት ስለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ባወጣው መግለጫ ሰልፍ እንዳይደረግ ከለከለ
- የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መንግስት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ጠየቀ
በዚህም ለፊታችን የካቲት 5 2015 የተጠራው ሰልፍ በቤተክርስቲያኗ አደባባዮች ያለማንም ጫና እንደሚካሄዱ በቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ ተጠቅሷል።
መንግስትም ድርሻው ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ብቻ መሆኑን ነው ያብራራው።
የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ትናንት ባወጣው መግለጫ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ሆነች “ህገወጥ ብላ የፈረጀችው ቡድን” የጠሩት ሰልፍ እንዳይካሄዱ መከልከሉ ይታወሳል።
ግብርሃይሉ ባወጣው መግለጫ "ህገወጥ የሰልፍ ጥሪዎች" ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ያለ ሲሆን፥ "በእምነቱ አባቶች በተመሳሳይ ቀንና ቦታ" የሰልፍ ጥሪ በማድረግ ግጭት የሚቀሰቅሱ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጿል።
መግለጫው "በሀይማኖት ሽፋን" የተጠራው ሰልፍ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ለማስተጓጎል ያለመ ስለመሆኑም ነው ያብራራው።
ማሳሰቢያውን በመተላለፍ ሰልፍ ለማድረግ በሚንቀሳቀስ አካል ላይም ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ግብረ ኃይሉ ማስጠንቀቁ የሚታወስ ነው።
ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ግን ከመንግሥት የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ቤተክርስቲያኗ ስለጠራችው ሰላማዊ ሰልፍ ያወጣውን መግለጫ ተቃውሟል።
መግለጫው “ህገወጡን ስብስብ ህጋዊ አድርጓል፤ የቤተክርስቲያኗን ህጋዊ መብትም ገፏል” ነው ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ።
ሰላማዊ ሰልፉን የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች የጠሩት አፍራሽ ድርጊት አድርጎ መሳልም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ እንዲታረም ጠይቋል።
ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህገመንግስታዊ መብት መሆኑን የጠቀሰው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ፥ መንግስት ላወጣው ህግና መመሪያ ተገዥ እንዲሆን አሳስቧል።
ቤተክርስቲያኗ አሁንም ለንግግር ዝግጁ መሆኗን የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶስ፥ ችግሩ የሚፈታበት መንገድ ግን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና መንፈሳዊ የአስተዳደር ሥርዓቶችን እንዳይጥስ አሳስቧል።
ቤተክርስቲያኗ መንግስት ሕግ እና ሥርዓትን እንዲያስከብርና በሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ በሚል ጸሎተ ምህላ ማወጇን ያወሳው መግለጫው፥ በአንጻሩ የማዋከቡ ስራ ተባብሶ መቀጠሉን ጠቁሟል።
መንግስት በሰከነ መንፈስ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ ንግግርን ምርጫው እንዲያደርግም ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።