ምክር ቤቱ ወለጋ ላይ የተገደሉ ዜጎችን ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲይዝ በአብን አባላት የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ
አባላቱ መደበኛ ስብሰባው በህሊና ጸሎት እንዲጀመርና የሃዘን ቀን እንዲታወጅ ጠይቀው ነበር
በዚህም የአብን የምክር ቤት አባላት ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የዛሬውን የምክር ቤቱን መደበኛ ስብሰባ ረግጠው ወጡ፡፡
አባላቱ ቃለ ጉባኤ ለማጽደቀና የኦዲት ሪፖርት ለማድመጥ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ/ም የተካሄደውን መደበኛ ስብሰባ ረግጠው የወጡት ምክር ቤቱ በወለጋ ጥቃት የሞቱ ዜጎችን ጉዳይ በአጀንዳነት ለመያዝ አለመፍቀዱን ተከትሎ ነው፡፡
በስብሰባው መጀመሪያ የአብን የባህርዳር ተወካይ የምክር ቤቱ አባልና የቀድሞው የድርጅቱ ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በወለጋ የተገደሉ ዜጎች ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲያዝ ጠይቀው ነበር፡፡
ጉዳዩን በአጀንዳነት መያዝ ብቻም ሳይሆን ስብሰባው በራሱ በህሊና ጸሎት ሊጀመር እና ብሔራዊ የሃዘን ቀን ሊታወጅ እንደሚገባውም ነው የአብን ተወካዮች የጠየቁት፡፡
ሆኖም ምክር ቤቱ ከተያዘው አጀንዳ ውጭ ሌላ አጀንዳ አይዝም ያሉት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ሌላ አጀንዳ ለማስያዝ የራሱ አሰራር እንዳለው በመግለጽ ጥቄውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡
አቶ ታገሰ “ባልተያዘ አጀንዳ ላይ አንወያይም፤ አጀንዳ ካለ የአማካሪ ኮሚቴ አባል ስለሆኑ በእሱ በኩል እንነጋገራለን” በማለት ነበር ጥያቀውን ሳይቀበሉ የቀሩት፡፡
ይህንን ተከትሎም አብንን ወክለው ም/ክር ቤት የገቡ አባላት ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል፡፡
የምክር ቤቱ የአብን አባላት ቀድመው በተስማሙት መሰረት ከሁለቱ አጀንዳዎች በፊት በወለጋና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚኖሩ አማራዎች ላይ እየተፈፀመ ያለውን “ጅምላ ግድያ፣ የዘር ማጽዳትና ፍጅት” ምክር ቤቱ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እንዲወያይበት መጠየቃቸውን ተናገሩት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ”አፈ ጉባዔው በመከልከላቸውና አፈና ስለተፈፀመብን ስብሰባውን አቋርጠን ለመውጣት ተገደናል” ብለዋል።
ስብሰባውን ረግጠው የወጡት የአብን የምክር ቤት አባላት የባህር ዳር ከተማ ተወካዩ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ የጅጋ ተወካዩ አቶ አበባው ደሳለው፣ የሸበል በረንታ-ዕድ ውሃ ተወካይ አቶ ሙሉቀን አሰፋ እና የጭስ አባይ ተወካዩ አቶ ዘመነ ሃይሉ ናቸው፡፡