ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ሲያሸንፉ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው
በጣልያን በተካሄደው ምርጫ ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች አሸነፉ።
የጣልያን ህግ አውጪ ምክር ቤት ለጠቅላይ ሚንስትር ማሪዮ ድራጊ የመተማመኛ ድምጽ መንፈጉን ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ከሁለት ወራት በፊት የጣልያን ፓርላም እንዲበተን እና አዲስ መንግስት በምርጫ እንዲመሰረት ውሳኔ አሳልፈው ነበር።
ይሄንንም ተከትሎ የጣልያም ፓርቲዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ በትናንትናው ዕለት አካሂደዋል።
በዚህ ምርጫ ላይ 51 ሚሊዮን ዜጎች ድምጽ መስጠት ቢችሉም 64 በመቶ ያህሉ ብቻ ድምጽ ሰጥተዋል ተብሏል።
የጣልያን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በአንጻራዊነት የተሻለ ድምጽ ያገኙ ሲሆን ይህም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
እነዚህ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በቀጣዮቹ ቀናት በትብብር መንግስት እንደሚመሰርቱ የሚጠበቅ ሲሆን የጣልያን ወንድማማቾች ፓርቲ መሪ የሆኑት ጆዎርጂያ ሜሎኒ የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
የጂዮርጂያ ሜሎኒ ፓርቲ ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ አራት በመቶ የመራጮችን ድምጽ አግኝቶ ነበር።
በአሁኑ ድል የቀናቸው የጣልያን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ለአውሮፓ ህብረት ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት አሉታዊ አመለካከት እንዳላቸው ይገለጻል።
ከሁለት ቀናት በፊት የአውሮፓ ህብረት በጣልያን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ዙሪያ ማስጠንቀቂያ ማውጣቱም ይታወሳል።
የአውሮፓ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ከሩሲያ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው የሚገለጽ ሲሆን እነዚህ ፓርቲዎች በአውሮፓ ህብረት የተጣሉ ማዕቀቦችን ላያከብሩ እንደሚችሉ ተሰግቷል።
አሁን ምርጫ ያሸነፉት የጣልያን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎችም ከምርጫው በፊት በነበሩ የምርጫ ቅስቀሳዎች ላይ እንዳሉት ስልጣን ከያዙ የጣልያን ዜጎችን የሚጎዱ አሰራሮችን እና ስምምነቶችን እንደማይቀበሉ ተናግረው ነበር።
በምርጫው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት መሰረት በሜሎኒ የሚመራው የጣልያን ወንድማማቾች ፓርቲ በአብላጫ ድምጽ ማሸነፉ የተገለጸ ሲሆን በጣልያን ታሪክ የመጀሙሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚንስትር ይሆናሉም ተብሏል።
በጣልያን ምርጫ ከተሳተፉ ሰዎች ውስጥ 51 በመቶዎቹ ሴቶች ሲሆኑ የ200 የሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ተጠናቋል።