ኢኳቶሪያል ጊኒን ለ43 ዓመታት የመሩት ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ለ6ኛ ጊዜ ምርጫ አሸነፉ
ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉዌማ 95 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል ተብሏል
ውጤቱ የ80 ዓመቱ ኦቢያንግ የ43 ዓመት የስልጣን ጊዜያቸውን በማራዘምና በአለም የረዥም ጊዜ ገዥነታቸውን አጠናክሯል
ኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉዌማ ከሳምንት በፊት በተደረገው ምርጫ 95 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል ተብሏል።
ፓርቲያቸው ሁሉንም የሴኔት እና የፓርላማ መቀመጫዎችን መያዙን ልጃቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ንጉሜ ኦቢያንግ ማንጌ በትዊተር ገፃቸው ላይ አሳውቀዋል።
ሮይተርስ ፕሬዚዳንቱ ዘድጋሚ መመረጣቸውን ወዲያውኑ ማረጋገጥ አልቻልኩም ብሏል።
ውጤቱ የ80 ዓመቱ ኦቢያንግ የ43 ዓመት የስልጣን ጊዜያቸውን በማራዘም እና በአለም የረዥም ጊዜ ገዥነት ቦታውን በማጠናከር ስድስተኛ የስልጣን ዘመን እንዲያገኙ አስችለሏቸዋል ነው የተባለው።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገፃቸው “የተረጋገጠው ውጤት ዳግም ትክክል መሆናችንን አረጋግጧል። ታላቅ የፖለቲካ ድርጅት መሆናችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ገዥው ፓርቲ የኢኳቶሪያል ጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲ እና ጥምረት ሙሉ በሙሉ 55 የሴኔት መቀመጫዎችን እና የተወካዮች ምክር ቤት በመባል የሚታወቀውን ም/ቤት 100 መቀመጫዎችን አሸንፏል። ፕሬዚዳንቱ አሁን የተቀሩትን 15 የሴኔት ወንበሮች መሾም ይችላሉ ሲል ልጃቸውና ምክትላቸው ተናግረዋል።
አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ያላት የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር እ.አ.አ በ1968 ከስፔን ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ሁለት መሪዎችን ብቻ አይታለች። ፕሬዝዳንት ኦቢያንግ በ1979 አጎታቸውን በመገልበጥ ስልጣን ከጨበጡ አራት አስርት ዓመታትን ተሻግረዋል።
ኦቢያንግ ሁሌም ከ90 በመቶ በላይ ድምጽ በማግኘት ምርጫን የሚያሸንፉ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ግን ቅቡልነቱ እምብዛም ነው።
ተቺዎች እንደሚሉት ኦቢያንግ ምርጫን በማጭበርበር ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት ያላደረጉት ጥረት የግል ሃብት ከማካበት የዘለለ አይደለም።
የመብት ተሟጋቾች ተቃውሞን በማፈን እና ተቀናቃኞችን በመጨፍለቅም ይከሷቸዋል። በሀገሪቱ ተቃውሞዎች በአብዛኛው የተከለከሉ ናቸው የሚሉት ተሟጋቾች፤ መገናኛ ብዙኸን በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ይታሰራሉ እና ይሰቃያሉ ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱ ተተኪ አንደሚሆኑ የሚጠባበቁት ም/ፕሬዚዳንቱ እ.አ.አ በ2020 የፈረንሣይ ፍ/ቤት ገንዘብ በማጭበርበር ጥፋተኛ ተብለዋል።
አባት እና ልጅ ምንም ጥፋት አልሰራንም በሚል ክሱን ክደዋል።