ኢንስቲትዩቱ እያሻቀበ ያለውን ኮቪድ 19 ለመግታት በህዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት የሚፈጠሩ መሰባሰቦች ኢንዲቀሩ ጠየቀ
አሁን ባለው ሁኔታ በሆስፒታሎች የአስተኝቶ ማከሚያ ክፍሎች፣ አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ እጥረት እያጋጠመ ነው
አዲሱ “ዴልታ” ቫይረስ በኢትዮጵያ መኖሩን ለማረጋገጥ የተለያዩ የልየታ ስራዎች እያከናወንኩ ነው
በኢትዮጵያ እያሻቀበ ያለውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመግታት ለመጪው የአዲስ ዓመት እና ሌሎች ህዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት የሚፈጠሩ መሰባሰቦች እንዲቀሩ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክረ ሀሳብ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዛሬው እለት ወቅታዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም ካለፉት 6 ወራት ወዲህ በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነስ ጋር ተያይዞ፤ በሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሰጠው ትኩረት እየቀነሰ መምጣት፣ ለበሽታው መሰራጨት ምቹ ሁኔታዎች መፍጠሩን አስታውቋል።
በተለያዩ ሐገራት ለተከሰተው 3ኛው የኮቪድ-19 ማዕበል እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው ኮቪድ-19 ቫይረስ እራሱን ወደ ተለያዩ አዳዲስ የቫይረስ ዓይነቶች መቀየሩ እንዲሁም “ዴልታ” የሚባለው የቫይረስ ዓይነት መሰራጨቱ መሆኑንም ገልጿል
ከዚህ ቀደም “አልፋ እና ቤታ” የቫይረስ ዓይነቶች በኢትዮጵያ መኖራቸውን እንደገለጸ ያስታወቀው ኢንስቲትዩቱ፤ ነገር ግን አዲሱ “ዴልታ” ቫይረስ መኖሩን ለማረጋገጥ የተለያዩ የልየታ ስራዎች እያከናወንኩ ነው ብሏል።
በአሁኑ ጊዜ ያለው የኮቪድ-19 ሃገራዊ ሁኔታን በተመለከተ፡-
በሆስፒታሎች የአስተኝቶ ማከሚያ ክፍሎች፣ አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ እጥረት እያጋጠመ መሆኑን ነው ኢንስቱትዩቱ በመግለጫው ያመለካተው።
በመሆኑም የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ሞት ለማስቆም ለመጪው የአዲስ ዓመት እና ሌሎች ህዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት የሚፈጠሩ መሰባሰቦችን ማስቀረት ተገቢ መሆኑን አመላክቷል።
ሁሉም ተቋማት ደንበኞቻቸውን የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን እንዲተገብሩ ማድረግ፣ የኮቪድ-19 ምልክቶች ሲታዩ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራ ማካሄድ፣ የኮቪድ-19 ክትባትን መከተብ፣ ከቤት ውጭ ስንንቀሳቀስ ማስክ ማድረግ፤ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር መያዝ እንዲሁም ያልበሰሉ የምግብ ተዋጽኦዎችን እንደ ጥሬ ሥጋ፣ ያልተፈላ ወተት እና ሌሎችን ከመመገብ መቆጠብ መልካም ነው በሏል።
ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመመሪያ 803/2013 ዓ/ም ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉም ጠይቋል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ 3ኛ ዙር የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ስለመከሰቱ ማሳያዎች ተገኝተዋል ማለታው ይታወሳል።