በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር ከ111 ቀናት በኋላ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል
በትናንት ከተመረመሩት 6 ሺህ 814 ውስጥ 1 ሺህ 6 ግለሰቦች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፤ ይህም ከተመረመሩት ውስጥ 15 በመቶ ነው የተገኘባቸው
21 ግለሰቦች በኮቪድ 19 ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ 463 ሰዎች ደግሞ በጽኑ የታመሙ መሆናቸውን ትናንት የወጣው ሪፖርት ያመለክታል
በትናንትናው ዕለት በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር ከ111 ቀናት በኋላ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ነሀሴ 14 ቀን 2013 ከተመረመሩት 6 ሺህ 814 ውስጥ 1 ሺህ 6 ግለሰቦች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፤ ይህም ከተመረመሩት 100 ግለሰቦች 15 ግለሰቦች ወይም (15%) መያዛቸው ተረጋግጧል።
ይህ በኮቪድ-19 የመያዝ ምጣኔ ከ107 ቀናት በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ መመዝገቡንም ነው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያስታወቀው።
በትላንትናው ዕለት 21 ግለሰቦች በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ 463 ሰዎች ደግሞ በጽኑ የታመሙ መሆናቸውንም አስታውቋል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ቫይረስ የሚያዙ ፤ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ እንዲሁም በኮቪድ -19 ህይወታቸውን የሚያጡ ግለሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
እያንዳንዱ ግለሰብ ፤ ቤተሰብ ፤ ሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፤ የሐይማኖት ተቋማት ፤ ሲቪክ ማህበራት ፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፤ የጤና ባለሙያዎች ፤ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ማስክ ማድረግ ፤ የእጃቸውን ንጽህና በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተገቢውን ጥንቃቄ እዲያደርጉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስስቧል።
በኢትዮጵያ እስካሁን 3 ሚሊየን 148 ሺህ 930 የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 293 ሺህ 737 ግለሰቦች ላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
በትላንትናው ዕለት በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ 21 ግለሰቦች ጨምሮ እስካሁን 4 ሺህ 539 ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል።