በሚኒስትርነት የተሾሙ የመጀመሪያዋ ቤተ እስራኤላዊት ሆነዋል
ፕኒና-ታማኖ-የመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት የእስራኤል ሚኒስትር
የ39 ዓመቷ ፕኒና ታማኖ ሻታ የእስራኤል የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፡፡ ይህ በእስራኤል ታሪክ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ የመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ብቻም ሳይሆን አፍሪካዊ ያደርጋቸዋል፡፡
በቤኒ ጋንዝ የሚመራው “ብሉ ኤንድ ኋይት”ፓርቲ ነው ለፕኒና የተጠቀሰውን ሹመት የሰጠው፡፡ በዬይር ላፒድ የሚመራውን “የሽ አቲድ”ፓርቲ ለቀው በቅርቡ “ብሉ ኤንድ ኋይት”ፓርቲን መቀላቀላቸውን ተከትሎ ነው ሹመቱን ሊያገኙ የቻሉት፡፡
“ብሉ ኤንድ ኋይት”ራሱን ችሎ መንግስት ለመመስረት ባለመቻሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኒታንያሁ ከሚመራው “ሊኩድ”ፓርቲ ጋር መጣመሩ የሚታወስ ነው፡፡
በ“የሽ አቲድ”ፓርቲ አባልነት ሳሉ በተቀላቀሉት የሃገሪቱ ፓርላማ (ክኔሴት) አሁንም አባል ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
ውልደትና እድገት
ፕኒና በ“ዘመቻ ሙሴ” በሱዳን በኩል ወደ እስራኤል ከተወሰዱ ቤተ እስራኤላውያን መካከል አንዷ ናቸው፡፡ በጎንደር አካባቢ ተወልደው ያደጉም ሲሆን የ3 ዓመት ህጻን ሳሉ ነው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ እስራኤል ያቀኑት፡፡ ያኔ የሃገሪቱ ጦር አዛዥ የነበሩት ቤኒ ጋንዝ ደግሞ ከዘመቻው መሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
በእስራኤል፣በአሜሪካ እና በሱዳን የስለላ ድርጅቶች ማለትም በሞሳድ፣ በሲ.አይ.ኤ እና በኤስ.ኤስ.ኤስ እንዲሁም በቅጥረኛ የዘመቻው አባላት በእስራኤል ጦር ታግዞ እ.ኤ.አ ከህዳር 21/1984 እስከ ጥር 5/1985 ገቢራዊ በሆነው “ዘመቻ ሙሴ” አስር ሺ ገደማ ቤተ እስራኤላውያን ከሃገር መውጣታቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ በአብዮት ደጋፊና ነቃፊ ትናጥ፤ በዚያድ ባሬ ጦር የመወረር አደጋ ውስጥም ወድቃ ነበረ፡፡
ከስደተኛ ቤተሰብ መካከል ወጥተው የእስራኤል ፓርላማ አባል እስከ መሆን የደረሱት ፕኒና በሙያቸው የህግ ጠበቃ፣ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ ናቸው፡፡
ፖለቲካዊ ህይወት
ዜና አንባቢ ከነበሩበት የጋዜጠኝነት ሙያ ወጥተው “የሽ አቲድ” ፓርቲን በመቀላቀል እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ የሃገሪቱን ፓርላማ ለተለያዩ አራት ያህል ጊዜያት አገልግለዋል፡፡ የመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት የፓርላማው አባልም ናቸው፡፡
ለመብቶች መከበር ባላቸው ተቆርቋሪነት እና ተሟጋችነትም ይታወቃሉ፡፡ የቤተ እስራኤላውያን መብት እንዲከበር ለማድረግም ብዙ ታግለዋል፡፡ ይህ ትግላቸው ፍሬ አፍርቶ ቤንያሚን ኒታንያሁን ጭምር ዋጋ እንዳስከፈለ ይነገራል፡፡
በእስራኤል የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረትን በከፍተኛ አመራርነት ካገለገሉ ቤተስራኤላውያን መካከልም አንዷ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ ከ1977 ጀምሮ በእስራኤል ጤና ሚኒስቴር ይተገበር የነበረውን የጤና ፖሊሲ ያስቀየሩ ጀግናም ናቸው፡፡ ፖሊሲው አፍሪካውያን ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ሊያስተላልፉ ይችላሉ በሚል ደም እንዳይለግሱ ይከለክል ነበረ፡፡ የዚህን ፖሊሲ ገፈትም ቀምሰዋል ጠንካራዋ ፕኒና፡፡ የኋላ ኋላ ግን እነ ፕሬዝዳንት ሺሞን ፔሬዝ ጭምር ሲያወግዙት የነበረው ፖሊሲ በእሳቸው ምክንያት እንዲሻሻልና እንዲቀየር ሆኗል፡፡
ልክ እንደ ፕኒና ሁሉ በ1991ዱ “ዘመቻ ሰለሞን” ከተወሰዱ ቤተ እስራኤላውያን መካከል አንዱ የሆኑት ደስታ ጋዲ የቫርካንም እንዲሁ በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት መሾማቸው ተሰምቷል፡፡
ከብሉ ኤንድ ኋይት ፓርቲ የፓርላማ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ አንዱ የነበሩት ጋዲ በቅርቡ ሊኩድን መቀላቀላቸው የሚታወስ ነው፡፡
ዘመቻ ሙሴን እና ዘመቻ ይሖዋ (ጆሽዋ) ተከትሎ በተካሄደው ዘመቻ ሰለሞን ከ14 ሺ በላይ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እየሩሳሌም ማቅናታቸው አይዘነጋም፡፡