በአማራና በአፋር ክልሎች ከ1 ሺህ 400 በላይ የጤና ተቋማት መጎዳታቸውን የጤና ሚንስቴር አስታወቀ
በርካታ ቁጥር ያላቸው አምቡላንሶች መውደማቸውንም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
ሚንስቴሩ የተጎዱ የጤና ተቋማት ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ተከትሎ በጤና ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በመግለጫቸው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ከ1 ሺህ 400 በላይ የጤና ተቋማት መጎዳታቸውን ገልጸዋል።
- “ሆስፒታሎች በግጭት ምክንያት የቆሰሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታካሚዎችን እያስተናገዱ ነው” የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ
- መንግስት አጋር ድርጅቶች ለአማራና አፋር ክልሎች የሚያደርጉትን ድጋፍ መጠን ከፍ እንዲያደርጉ ጠየቀ
በአማራ ክልል አምስት ዞኖች ማለትም ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ዋግ ኽምራ፣ ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በአጠቃላይ 20 ሆስፒታል 277 የጤና ተቋማት ከ1ሺህ በላይ የጤና ኬላዎች በጦርነቱ መጎዳታቸው ተገልጿል።
በአፋር ክልል ደግሞ አንድ ሆስፒታል፣ 10 ጤና ጣቢያ፣ 38 የጤና ኬላዎች መጎዳታቸውንም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጎች የተፈናቀሉ ሲሆን፤ በተለይም ህጻናት እና የሚያጠቡ እናቶች ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ወደ አገልግሎት ለማስጀመር ሚንስቴሩ የህክምና ቁሳቁስ፣ ገንዘብ፣ የሰው ሀይል እና ሌሎች ድጋፎችን ለሁለቱም ክልሎች በማድረግ ላይ መሆኑንም አስታውቋል።
ይሁንና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለጤና ተቋማቱ መጎዳት ኃላፊነት የሚወስደው ማን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሃት አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች ሆንብሎ ህወሃት ማውደሙን መግለጻቸው ይታወሳል።
የህወሃት ታጣቂዎች ሴቶችን፤ህጻናቶችን ጨምሮ ንጽሃን በአፋርና በአማራ ክልል በሀይል ተፈናቅለዋል፤ ኑሯቸው ተመስቃቅሏል ሲሉም በድብዳቤያቸው አስፍረዋል።
የፌደራል መንግስት ግጭቱን በውይይት ለመፍታት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ጦሩን ክትግራይ ክልል ቢያስወጣም፤ ግጭቱ ሊቆም አልቻለም። በትግራይ ክልል የተጀመረው ግጭት አሁን ላይ ወደ አፋርና አማራ ክልል ሊስፋፋ ችሏል።
የፌራል መንግስት፤ ተኩስ አቁም የተፈለገውን ተኩስ አቁም ባለማምጣቱ፤ መከላከያና የክልል ልዩ ኃይሎች በህወሃት ሃይሎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ አዞ፤ ጦርነቱ እየተካሄደ ይገኛል።
አሜሪካን ጨምሮ አለምአቀፍ ማህበረሰብ የፌደራል መንግትና ህወሓት ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ጫና በማሳደር ላይ ናቸው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ከሚሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በግለሰቦች ላይ ማእቀብ መጣል የሚያስችል ትእዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሰብአዊ ድጋፍ እንዲፈልጉ እና ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።