ክትባቱ በቅድሚያ “ከቢሮ ውጪ ሆነው ከህብረተሰቡ ጋር በቀጥታ ተገናኝተው ዘገባዎችን ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ይሰጣል” ተብሏል
ኢትዮጵያ ከመጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የአስትራ ዜኒካ ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ የመስጠት መርሐ ግብርን በይፋ ማስጀመሯ ይታወሳል።
ክትባቱን በቅድሚያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በስራ ላይ ላሉ ለጤና ባለሙያዎች በመስጠት ላይ ሲሆን ከትናንት ጀምሮ ደግሞ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ እና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ዜጎች ከትባቱን በመውሰድ ላይ ናቸው።
በቀጣይ ደግሞ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በሂደት ክትባቱ መሰጠት እንደሚጀምሩ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አል ዐይን አማርኛ ጋዜጠኞች ኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ ዋነኞቹ እንደመሆናቸው መጠን ክትባቱን መቼ ያገኛሉ? ሲል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ጠይቋል።
በሚኒስቴሩ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ብሔራዊ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሙሉቀን ዮሀንስ “ጋዜጠኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሚባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ይካተታሉ” ብለዋል።
በዚህም መሰረት “በቀጣይ ክትባቱ ይሰጣል” ያሉት ዶ/ር ሙሉቀን “ከቢሮ ውጪ ሆነው ከህብረተሰቡ ጋር በቀጥታ ተገናኝተው ዘገባዎችን ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ይሰጣል” ብለዋል።
ክትባቱ ለሁሉም ጋዜጠኞች የማይሰጠው “ያለው የክትባት መጠን አነስተኛ በመሆኑ” እንደሆነም ነው አስተባባሪው የተናገሩት፡፡
ክትባቱን በመንግስትም ይሁን በግል ብዙሃን መገናኛ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ተጋላጭ ጋዜጠኞችን ለመለየት እና ለመስጠት ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም ዶ/ር ሙሉቀን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በስራቸው ምክንያት በርካታ ጋዜጠኞች በቫይረሱ እየተጠቁ መሆኑ ይነገራል።
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ጥምረት ሃገራት ለጋዜጠኞች የኮሮና ቫይረስ ክትባት በቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡
ኬንያ እና ዚምባብዌም ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ባሳለፍነው ሳምንት ክትባቱን ለጋዜጠኞቻቸው መስጠት ጀምረዋል።