90 በመቶ የመከላከል ውጤታማነቱ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መገኘቱ ተገለጸ
ክትባቱ እስካሁን በሙከራ ላይ ከሚገኙት ስኬታማ የተባለ ሲሆን ከቀናት በኋላ ለቫይረሱ ተጋላጮች እንደሚሰጥ ተገልጿል
ክትባቱን ያገኘው ‘ፋይዘር’ የተሰኘው ኩባንያ “ዛሬ ለሳይንስ እና ለሰው ልጆች ትልቅ ቀን ነው” ብሏል
90 በመቶ የመከላከል ውጤታማነቱ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መገኘቱ ተገለጸ
‘ፋይዘር’ በተሰኘ የአሜሪካ መድኃኒት አምራች ኩባንያ 90 በመቶ ተከላካይነቱ የተረጋገጠ የኮሮናቫይረስ ክትባት ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የኩባንያው ዜና ተስፋን ያጫረ ሲሆን ኩባንያው ባወጣው መግለጫ “ዛሬ ለሳይንስ እና ለሰው ልጆች ትልቅ ቀን ነው” ብሏል፡፡
ክትባቱ 43500 ሰዎች ላይ ሙከራ ተደርጎ ውጤታማነቱ መረጋገጡን የጠቀሰው ኩባንያው እንደ አውሮፓውያኑ በዚህ ወር መጨረሻ የቫይረሱ ተጋላጮች እንዲከተቡት ለማድረግ መታቀዱንም አስታውቋል፡፡
የኮሮናን ክትባት ማግኘት ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚጣሉ እገዳዎችን ጨምሮ በሀገራት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ቀላል እንደሚያደርግ አሊያም እንደሚያስቀር ይታመናል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ሙከራ ላይ የሚገኙ በርካታ የቫይረሱ ክትባቶች በተለያዩ ሀገራት በምርምር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ፋይዘር ይፋ ያደረገው የአሁኑ ክትባት ከሁሉም በላይ ስኬታማው ነው ተብሏል፡፡
ዘ ናሽናል እንደዘገበው ክትባቱ ለሰዎች እንዲሰጥ በሚመለከታቸው አካላት ከተወሰነ እስከ 2021 መጨረሻ ድረስ 1.35 ቢሊዮን የክትባት መጠን (ዶዝ) እንደሚመረት ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ይፋ የተደረገው ክትባት እንደ ትኩሳት ያሉ ቀለል ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንደሚያስከትል ቢረጋገጥም በሌሎች ክትባቶች ከሚስተዋለው አንጻር ሲታይ ከባድ የሚባል አይደለም፡፡
የክትባቱ ሶስተኛ ደረጃ ሙከራ አሁንም ድረስ የቀጠለ ሲሆን በቅርቡ ተጨማሪ ማብራሪያዎች ይሰጡበታል ተብሏል፡፡