20 የአፍሪካ ሃገራት በቀጣዩ ሳምንት የኮሮና ክትባቶችን እንደሚያገኙ ይጠበቃል
ኢትዮጵያ ከ20ዎቹ ሃገራት መካከል ስለመሆኗ ማዕከሉ ያሳወቀው ነገር የለም
አፍሪካ ሲዲሲ 1 ሚሊዬን ክትባት በመጪው ሳምንት ወደ አህጉሪቱ እንደሚገባ አስታውቋል
የአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) በቀጣዩ ሳምንት ለ20 የአፍሪካ ሃገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን እንደሚከፋፍል አስታወቀ፡፡
ክትባቶቹ በህንድ የተመረቱ የአስትራዜናካ ክትባቶች ናቸው ያሉት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ የመጀመሪያዎቹ ሚሊዬን ክትባቶች ከሳምንት አርብ ወዲህ ለሃገራቱ ይደርሳሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ክትባቶቹ ኤምቲኤን በተባለው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ድጋፍ የተገዙ ናቸው፡፡
ኤምቲኤን 7 ሚሊዬን ገደማ ክትባቶችን ለመግዛት የሚያስችል የ25 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከ7 ሚሊዬኑ መካከል በመጪው ሳምንት ቀድሞ ወደ አህጉሪቱ እንደሚገባ የሚጠበቀው 1 ሚሊዬን ክትባትም ነው ለ20ዎቹ ሃገራት ይከፋፈላል የተባለው፡፡
ክትባቱ በከፍተኛ የወረርሽኙ የተጋላጭነት ደረጃ ለይ ለሚገኙ የጤና ሰራተኞች እና ለሌሎችም የሚሰጥ ነው፡፡
ክትባቱን ቀድመው የሚያገኙት 20ዎቹ ሃገራት የትኞቹ እንደሆኑ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ከሃገራቱ መካከል ትሁን አትሁንም አልታወቀም፡፡
በመጋቢት መጨረሻ ጀምሮ ክትባቶችን ሃገር ውስጥ ማስገባት እንደሚጀምር ጤና ሚኒስቴር ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ባቋቋመው የክትባት ግብረ ኃይል በኩል ከአህጉሪቱ ህዝብ 60 በመቶ ያህሉን ለመከተብ የሚያስችሉ 670 ሚሊዬን ገደማ ክትባቶችን ለማግኘት እየሰራ ነው፡፡
የአስትራዜናካ ክትባቶች ቫይረሱን የመከላከል ዐቅም በተለይም አዲስ ነው የሚባለውን የቫይረሱን የዝርያ ዓይነት መከላከል ላይ እጥረት እንዳለባቸው ይነገራል፡፡
ክትባቶቹን መጠቀም ጀምራ የነበረችው ደቡብ አፍሪካም በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተመረቱትን መጠቀም ጀምራለች፡፡
ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ ግን ምናልባት በአየር ሁኔታ ለውጦች ካልሆነ በስተቀር የክትባቱን ውጤታማነት ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዬን የሚበልጡ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ የ1 መቶ 294 ሺ ሰዎች ህይወት ያለፈም ሲሆን ከ3.3 የሚልቁ ህመምተኞች አገግመዋል፡፡