ኢትሃድ አየር መንገድ ሰራተኞቹን በሙሉ የኮሮና ክትባት የከተበ የመጀመሪያው አየር መንገድ ሆነ
ዩኤኢ ክትባቱን ፈጥነው ለመስጠት ከቻሉ የዓለማችን ሃገራት ሁለተኛዋ ነች
አየር መንገዱ ይህን ያደረገው የሰራተኞቹን ደህንነት በማረጋገጥ ለደንበኞቹ ጤና ዋስትና ለመስጠት ነው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ብሄራዊ አየር መንገድ የሆነው ኢትሃድ አየር መንገድ የበረራ ክፍል አባላቱን ጨምሮ ሰራተኞቹን በሙሉ የኮሮና ክትባት የከተበ የመጀመሪያው የዓለማችን አየር መንገድ ሆነ፡፡
አየር መንገዱ ይህን ያደረገው የሰራተኞቹን ደህንነት በማረጋገጥ ለደንበኞቹ ጤና ዋስትና ለመስጠት ነው፡፡
በዘርፉ የተቀመጡ ከፍተኛ የንጽህና ደረጃዎችን ላቅ ባለ ሁኔታ በማሟላቱም ባሳለፍነው ወር ጥር የአልማዝ (ዳይመንድ) ደረጃን ከአፔክስ ሄልዝ እና ከሴፍቲ ኦዲት አግኝቷል፡፡
የሰራተኞቹን እና የተገልጋዮቹን ደህንነት ለመጠበቅ የተከተለው የክትባት መርሃ ግብርም በዘርፉ ቀዳሚ አድርጎታል፡፡
የአየር መንገድ ግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቶኒ ዳግላስ ክትባቱን በቶሎ ለሁሉም ሰራተኞቻችን ሰጥተናል ብለዋል የቫይረሱን ተጽዕኖዎች ለማቅለል እና የደንበኞችን ደህንነትና አብሮነት ለማረጋገጥ በማሰብ የተደረገ መሆኑን በመግለጽ፡፡
አየር መንገዱ ከየትኛውም በረራ በፊት ደንበኞቹ እና የበረራ ክፍል ሰራተኞቹ የቫይረሱን ምርመራ እንዲያደርጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ቀዳሚ የዓለማችን አየር መንገድ ነው፡፡
አሁንም ሙሉ ሰራተኞቹን በመከተብ ቀዳሚ ሆኗል እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ፡፡
ውጤቱ “በጋራ እንጠበቅ” “Protected Together” በሚል ተነሳሽነት ባሳለፍነው ወር በተደረገ የአየር መንገዱን ሰራተኞች የመከተብ ዘመቻ የተገኘ ነው፡፡
ዘመቻው ዩኤኢ ተግበራው ከነበረው “ክትባትን እንምረጥ” መርሃግብር ጋር ተጣጥሞም ተተግብሯል፡፡
አየር መንገዱ ከአሁን ቀደምም ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ ሰራተኞቹ ክትባቱን ቀድመው እንዲያገኙ አድርጓል፡፡
ዩኤኢ እስከ መጪው ወርሃ መጋቢት መጨረሻ ከአጠቃላይ ህዝቧ ግማሽ ያህሉን ለመከተብ አቅዳ በመስራት ላይ ነች፡፡
ከዕቅዷ ቀድማም ከአጠቃላይ ሰራተኛ ኃይሏ 65 በመቶ ያህሉ ቢያንስ አንድ ጊዜ ክትባቱን እንዲያገኙ ለማድረግም ችላለች፡፡
ዩኤኢ ክትባቱን ፈጥነው ለመስጠት ከቻሉ የዓለማችን ሃገራት ሁለተኛ መሆኗንም ነው የአል ዐይን አረብኛ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡