ወረርሽኞችን የተመለከተ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ስምምነት ሊደረግ እንደሚገባ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አሳሰቡ
ስምምነቱን የተመለከተ ምክክር በመጪው ህዳር ሊደረግ እንደሚችልም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል
ዶ/ር ቴድሮስ መረጃዎችን፣ የምርምር ውጤቶችንና ሌሎችንም ለማጋራት አለመቻሉ የበለጠ ለኮሮና ወረርሽኝ አጋልጧል ብለዋል
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ወረርሽኞችን የተመለከተ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ስምምነት ሊደረግ እንደሚገባ አሳሰቡ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የፈጠረው አደጋ አብቅቷል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድ ስህተት ነው ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ ሲካሄድ በነበረው የድርጅቱ ጉባኤ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የኮሮና ወረርሽኝ የስርጭት እና የሞት ሁኔታዎች ላይ መሻሻሎች እየታዩ ቢሆንም አሁንም ከወረርሽኙ መውጫ መንገድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መንገዱ ደግሞ ሁሉም የድርጅቱ አባል ሃገራት የተካተቱበት ዓለም አቀፍ የወረርሽኝ ዝግጁነት ስምምነት ማድረግ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ የኮሮና ወረርሽኝ የተመለከቱ መረጃዎችን ለመጋራት፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ትብብር ለማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት የከፋ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
ይህን ክፍተት ለመሙላትና ድርጅቱ ያሉበትን የፋይናንስ ችግሮች ለመቅረፍ አባል ሃገራቱ መስማማት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡
መስማማቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ለመስጠት፣ ለማጋራት፣ ቅድመ ዝግጅትን ለማድረግና የመድሃኒት እና ክትባቶች ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ያስችላል እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡
ስምምነቱን የተመለከተ ምክክር የድርጀቱ አባል ሃገራት ጉባዔ በሚካሄድበት ወቅት በመጪው ህዳር ላይ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
ስምምነቱ “አካታችና ሁሉም በወጉ የሚወከልበት ሊሆን ይገባልም ነው”ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ፡፡
አባል ሃገራቱ እስከ መጪው መስከረም ድረስ ቢያንስ ከአጠቃላዩ የዓለም ህዝብ 10 በመቶ ያህሉን፤ እስከ ዓመቱ መጠናቀቂያ (ጥር ድረስ) ደግሞ 30 በመቶ ያህሉን እንዲከትቡም አሳስበዋል፡፡
እስከ ትናንት ድረስ 169.5 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የሚያመለክተው የድርጅቱ የኮሮና መረጃ የ3.5 ሚሊዬን ሰዎች ህይወት ማለፉን ይጠቁማል፡፡
እስካሳለፍነው አርብ ድረስ ከ1.5 ቢሊዮን በላይ የኮሮና ክትባቶች ጥቅም ላይ መዋላቸውንም መረጃው ያመለክታል፡፡