ህንድ ከቀዳሚዎች የዓለማችን ክትባት አምራቾች ተርታ ነች
አስከፊው የህንድ የኮሮና ወረርሽኝ ቀውስ የአፍሪካን የክትባት አቅርቦት ጎድቷል ተባለ፡፡
የወረርሽኙን መክፋት ተከትሎ ህንድ በሃገሯ ተመርተው ለውጭ የሚቀርቡ ክትባቶችን አግዳለች፡፡
ይህ እስካሁን በወረርሽኙ ክትባት እምብዛም ያልገፋችውን አፍሪካን የሚጎዳ ነው፡፡
60 በመቶ ያል ህዝቧን ለመከተብ ያሰበችው አፍሪካ እስካሁን 2 በመቶ ያህሉን እንኳ አልከተበችም፡፡
ሴረም በተባለው ህንድ የመድሃኒቶች አምራች ድርጅት የተመረቱ የአስትራ ዜኔካ የኮሮና ክትባቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በኮቫክስ ስርዓት በታቀፉ የተለያዩ ሃገራት ደርሰዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ አፍሪካውያን ተከትበውም ነበረ፡፡
ሆኖም አሁን ክትባቶቹ የሉም፡፡
በኮቫክስ የግዢ ስርዓት በመታቀፍ 20 በመቶ ያህል ህዝባቸውን ለመከተብ አቅደው የነበሩ የፍሪካ ሃገራትን በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉት 41 ሃገራትን ይጎዳል፡፡
የከፋ ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ድቀትን ሊያስከትል እንደሚችልም ነው የሚነገረው፡፡
የአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ዳይሬክተር ዶ/ር ኔኬንጋሶንግ እንደ አህጉር የገጠመውን ችግር ለመሻገር ሶስት አማራጮችን መከተሉ የሚበጅ ነው ይላሉ፡፡
አማራጮቹ የመመርመር፣ የመከላከል አቅምን እንዲሁም የክትባት እና የኦክስጂን አቅርቦትን ማሳደግ የሚሉ ናቸው፡፡
በቅርቡ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ የወባ በሽታ ክትባት መገኘቱም እንደ አህጉር ያለውን የክትባት ተስፋ ከፍ አድርጎታል፡፡
እስካሁን እንደ አህጉር ከቀረበው አጠቃላይ 38 ሚሊዬን ክትባት ውስጥ 22.4 ሚሊዬን ያህሉ አገልግሎት ላይ መዋሉን ማዕከሉ አስታውቋል፡፡
ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ እና ኢትዮጵያ ከቀረበላቸው ክትባት ውስጥ አብዛኛውን በመከተብ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡