አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ በኮቪድ 19 መያዛቸውን አስታወቁ
ፕሬዝዳንቱ “የሶማሊያ ህዝብ የጤና ባለሙያዎች ምክሮችን በመከተል ሁሉም ሰው ራሱን ይጠብቅ” ብለዋል
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ “ህዝቤን ከቤት ሆኜ ማገልገሌን እቀጥላለሁ” ብለዋል
በኮቪድ-19 የተያዙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ “ህዝቤን ከቤት ሆኜ ማገልገሌን እቀጥላለሁ” አሉ።
ፕሬዝዳንቱ ከደቂቃዎች በፊት በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) መያዛቸውን አስታውቀዋል።
“በኮቪድ ብያዝም እስካሁን ምንም አይነት ምልክት የለኝም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ራሳቸውን ማግለላቸውም ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ “የሶማሊያን ህዝብ ከቤት ሆኜ ማገልገሌን እቀጥላለሁ” በማለት የተለመደውን የመሪነት ኃላፊነት እንደሚወጡ ለህዝባቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ለህዝባቸው ባስተላለፉት መልእክት፡ “ጤና ባለሙያዎች ምክሮችን እና መመሪያዎችን በመከተል ሁላችን ራሳችንን እንጠብቅ” ብለዋል።
በቅርቡ የሶማሊያ ፕሬዝዳንትነት በትረ ስልጣን የተቆጣጠሩት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ “ሰላም የሰፈነባት እና ከዓለም ጋር ሰላም ያላት ሀገር ለማድረግ እሰራለሁ” ሲሉ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ የሚያጋልጥ ከባድ ድርቅን ጨምሮ ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮች ያሉባት ሀገረ ሶማሊያ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ቀላል የቤት ስራ ይዛ እንደማትቆይ እየተነገረ ነው።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ሰላማዊ ሶማሊያን እውን ለማድረግ ለወራት በዘለቀው የፖለቲካ ትርምስ እና የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ በአስፈጻሚ ደረጃም ሆነ በማዕከላዊ መንግስት እና በክልል ባለስልጣናት መካከል ያለውን የግንኙነት መሻከር ማስተከከል እንደሚጠበቅባቸውም በርካቶች ያነሳሉ።