በፔሩ ሪፖርት ከተደረገው በላይ ሰዎች በኮሮና ምክንያት ሞተዋል ተባለ
ፔሩ ይህን ያደረገችው ተመራማሪዎች ሪፖርቱን የተመለከተ ምክረ ሃሳብ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው
69 ሺ ያህል ዜጎቿ በኮሮና ምክንያት መሞታቸውን ሪፖርት አድርጋ የነበረችው ፔሩ የሟቾቹን ቁጥር ወደ 180 ሺ ከፍ አድርጋለች
ፔሩ በኮቪድ 19 ሳቢያ በሀገሪቱ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥርን በእጥፍ ከፍ ማድረጓ ተሰምቷል።
ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 69 ሺህ 342 በሚል ይፋ አድርጋ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ባደረገችው ማስተካከያ ግን ወደ 180 ሺህ ከፍ አድርጋለች።
የፔሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቫዮልታ ቤርሙዴዝ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከፍ የተደረገው የፔሩ እና የዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ምክርን ተከትሎ ነው ብለዋል።
“አሁን በሀገሪቱ የተከሰተው ሞት ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝበናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ይህም እኛ ከገመትነው በላይ የበርካታ ሰዎች ህይወት እያለፈ መሆኑን ያመላክታል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቫዮልታ አክለውም፤ “ለህዝባችን ትክክለኛ መረጃን ማቀበል ስራችን ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
የፔሩ የህክምና ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጎዶፌርዶ ተላቬራ፤ “የሟቾች ቁጥር ላይ በዚህ መጠን ለውጥ መደረጉ ሊያስገርም አይገባም” ብለዋል።
ከኦክሲጂን ጋር በታያያዘ ከመንግስተ በኩል ድጋፍ አልነበረንም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የጽኑ ህሙማን አልጋ እጥረት እንዲሁም በቂ ክትባት አለማግኘት ለቁጥሩ ማሻቀብ እንደዋነኛ ምክንያትነት አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም በፔሩ በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል በሚል ይፋ የተደረገው ቁጥር 69 ሺህ 764 የነበረ ሲሆን፤ አሁን በተደረገው ማስተካከያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 180 ሺህ 764 ነው።
አሁን በወጣው ሪፖርት መሰረትም በፔሩ ያለው የኮቪድ 19 የሞት ምጣኔ ከ100 ሺህ ሰዎች 500 ሰዎች በኮቪድ ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ያመላክታል።