ኢንዶኔዥያ ለእስረኞች የተዘጋጁ የኮሮና ክትባቶችን ሰርቀው የሸጡ 4 ሰዎችን ያዘች
ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ እድሜ ይፍታህ ሊጠብቃቸው እንደሚችልም ነው የተነገረው
ከተያዙት መካከል የህክምና ዶክተር ይገኝበታል ተብሏል
ለእስረኞች የተዘጋጁ የኮሮና ክትባቶችን ሰርቀው የሸጡ 4 ሰዎችን መያዟን ኢንዶዜዥያ አስታወቀች፡፡
ሰዎቹ እስረኞችን ለመከተብ ከተዘጋጁ ቻይና ሰራሽ የሲኖ ፋርም ክትባቶች ውስጥ 1 ሺ ያህሉን በመስረቅ በጃካርታ እና በሰሜናዊ ሱማትራ ሜዳን ከተማ አንዱን በ17 ዶላር (በ250 ሺ የሃገሪቱ ገንዘብ) ሲሸጡ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
ከተያዙት መካከል በሜዳን ከተማ ማረሚያ ቤት ያገለግል የነበረ የህክምና ዶክተር መሆኑ ተነግሯል፡፡
ጥፋተኝነታቸው በህግ የሚረጋገጥ ከሆነ በሃገሪቱ የጸረ ሙስና ህግ መሰረት እድሜ ይፍታህ ሊጠብቃቸው ይችላል ሲልም ነው ኤ ኤፍ ፒ የዘገበው፡፡
ኢንዶኔዥያ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጠቁ የደቡብ ምስራቃዊ እስያ ሃገራት መካከል አንዷናት፡፡
1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች በቫይረሱ የተያዙም ሲሆን የ50 ሺ ገደማ ሰዎች ህይወት ማለፉ ሪፖርት ተደርጓል፡፡
ይህን ተከትሎ 270 ሚሊዮን እንደሚጠጋ የሚገመተውን ዜጋዋን ለመከተብ ሰፊ የኮሮና ክትባት ዘመቻዎችን ጀምራለች፡፡
ሆኖም ክትባቶቹን በቅድሚያ የሚያገኙት በፊት አውራሪነት ወረርሽኙን በመዋጋት ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ በእድሜ የገፉ ዜጎች መሆኑንና የክትባቶች አቅርቦት እጥረት መኖሩን ተከትሎ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
ክትባቶቹ በነጻ ነው የሚሰጡት፡፡