ክትባቶቹ በቀዳሚነት ተጋላጭ ለሆኑ የህክምና ባለሙያዎች እና ሌሎችም ይሰጣል የተባለ ሲሆን ከፍተኛ ባለስልጣናት ቀድመው እንደሚከተቡም ይጠበቃል
ከነገ በስቲያ ቅዳሜ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የኮሮና ክትባቶችን መስጠት እንደሚጀምር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ በሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የኮቪድ-19 ክትባት የመስጠቱ መርኃ ግብር በይፋ ይጀመራል ብሏል።
ክትባቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወንኩ ነው ያለም ሲሆን ስልጠናዎች መሰጠታቸውን፣ ክትባቱን ማሰራጨትና ክትባቱን መውሰድ የሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መለየታቸውንም አስታውቋል፡፡
ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች፣ እድሜያቸው ከፍ ያሉ እና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን እንዲያገኙ ይደረጋልም ነው ሚኒስቴሩ ያለው፡፡
ለሌሎች አርዓያ እንዲሆኑ በማሰብ ክትባቱ ቀድሞ ለከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው እሁድ በኮቫክስ የግዢ ስርዓት ያገኘቻቸውን 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአስትራ ዜናካ ክትባቶች መቀበሏ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እስከ ወርሃ ሚያዚያ መጨረሻ ድረስ 7 ነጥብ 6 ሚሊዬን ዶዝ ክትባቶችን ትቀበላለች ነው የሚባለው፡፡ ለዚህ የሚሆነው 13 ቢሊዬን ብር ከተለያዩ የፋይናንስ ምንጮች መገኘቱም ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ሚሊዬን ከሚልቀው አጠቃላይ ህዝቧ 20 በመቶ ያህሉን የመከተብ እቅድ አላት መባሉ አይዘነጋም፡፡