እስካሁን ጥቅም ላይ ከዋሉ 210 ሚሊዬን የኮሮና ክትባቶች ግማሽ ያህሉን የተጠቀሙት ከ2 የማይበልጡ ሃገራት ናቸው ተባለ
ክትባቶቹ በመጪው ሳምንት ኮትዲቯር ይደርሳሉም ተብሏል
የመጀመሪያዎቹ 600 ሺ የኮቫክስ ክትባቶች ጋና ደርሰዋል
ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ92 ሃገራት እንደሚደርሱ ከሚጠበቁት የኮቫክስ ክትባቶች የመጀመሪያዎቹ 600 ሺ ክትባቶች ጋና ደረሱ፡፡
ክትባቶቹ በህንዱ የመድሃኒቶች አምራች ተቋም ሴረም የተመረቱ የአስትራዜናካ/ኦክስፎርድ ክትባቶች ናቸው የተባለ ሲሆን ከሙምባይ ተጭነው ዛሬ ጋና አክራ መድረሳቸው ተነግሯል፡፡
ይህም ጋናን በዓለም አቀፉ የክትባቶች ትብብር (ጋቪ) በተዘረጋው አዲስ የፋይናንስ ስርዓት (ኮቫክስ) የተቀበለች የመጀመሪያዋ ሃገር ያደርጋታል፡፡
በስርዓቱ ከታቀፉ የአፍሪካ ሃገራት መካከልም ቀዳሚዋ ናት ጋና፡፡
በመጪው አርብ ለወረርሽኙ የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎቿን መከተብ ለመጀመር ማቀዷንም ነው ጋና ያስታወቀችው፡፡
ከጋና ቀጥላ ክትባቶቹን የምታገኘው ኮትዲቯር ነች ተብሏል፡፡ ክትባቶቹ በዚህ ሳምንት ዋና ከተማዋ አቢጃን እንደሚደርሱም ነው ጋቪ ያስታወቀው፡፡
የኮቫክስ ስርዓት ክትባቶችን የመከተቢያ መርፌዎችን ጭምር በፍትሃዊነት ለማድረስ በማሰብ ነው የተዘረጋው፡፡
በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ 2 ነጥብ 3 ቢሊዬን ክትባቶችን መስፈርቶችን አሟልተው በስርዓቱ ለታቀፉ ሃገራት ለማድረስም ታስቧል፡፡
ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ቢሊዬን ያሉ ክትባቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ምጣኔ ሃብት ላላቸው 92 የዓለማችን ሃገራት በነጻ የሚሰጥ ነው፡፡
ያደጉ የሚባሉት የዓለማችን ሃገራት ለዜጎቻቸው የሚሆኑ ክትባቶችን ገዝተዋል፡፡ ለመግዛት በመጣደፍ ላይ ያሉም ጥቂት አይደሉም፡፡
በመላው ዓለም እስካሁን 210 ሚሊዬን ክትባቶች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ሆኖም ከነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉን ከሁለት የማይበልጡ ሃገራት ናቸው የተጠቀሙት፡፡
አንዲቷንም ክትባት እንኳን ያላገኙ ከ200 የሚበልጡ ሃገራት እንዳሉ ነው ሃገራት ሊተባበሩ እንደሚገባ ያሳሰቡት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የተናገሩት፡፡