በአውሮፓ በኤትኤሞች ላይ የሚደረግ የገንዘብ ዝርፊያ መበራከቱ ተሰማ
ባንኮች የኤትኤሞችን ደህንንት ለማጠናከር ከ300 ሚሊየን ዩሮ በላይ ወጪ አድርገዋል
ባንኮችን በመዝረፍ አደጋ ላይ መውደቅ ያልፈለጉ የተደራጁ ዘራፊዎች በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ማሽኖቹን ኢላማ እድርገዋል
በአውሮፓ የተለያዩ ሀገራት በኤትኤም ማሽኖች ላይ ያነጣጠረ ዝርፍያ መበራከቱ ተሰምቷል፡፡
በዋናነት በጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድ እየተስፋፋ ይገኛል የተባለው ወንጀል ከ2022 ጀምሮ በተለያዩ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች እየተፈጸመ ነው ተብሏል፡፡
ዘራፊዎቹ ኤቲኤሞቹን በተለያዩ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች በማፈንዳት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ዘረፋ መፈጸማቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
- የመረጃ መንታፊዎች የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትርን ጨምሮ ከ3500 በላይ የባንክ ሂሳቦች ላይ የሳይበር ጥቃት መፈጸማቸው ተገለጸ
- ሐሰተኛ የባንክ ቅርንጫፍ ቢሮ ከፍተው የሚያጭበረብሩት ሌቦች
በአውሮፓ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆነችው ጀርመን የጥሬ ገንዘብ ክፍያ ከፍተኛ ድርሻ የሚወስድ መሆኑን ተከትሎ በአንድ ኪሎ ሜትር ልዩነት አንድ ኤትኤም ይገኛል፡፡
በዚህም ከ51 ሺህ በላይ ኤቲኤሞች በሚገኝባት ሀገር በ2023 ከ461 በላይ ኤትኤሞች የተዘረፉ ሲሆን የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ደግሞ በሀገሪቱ በቀን ከአንድ በላይ የኤቲኤም ማሽን ዝርፍያ እንደሚፈጸም ያመላክታሉ፡፡
በአንጻሩ 5 ሺህ ኤቲኤሞች ያሏት ኔዘርላንድ በቁጥር አነስተኛ ማሽኖች ቢኖራትም በወንጀል ምጣኔው ከጀርመን ቀጥላ በሁለተኛነት ትገኛለች፡፡
ዩሮ ፖል እነዚህን የተደራጁ ወንጀለኞች ተከታትሎ ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ሲሆን ወንጀሎቹ የሚፈጸምባቸው ስፍራዎች ህዝብ በማይበዛባቸው አካባቢዎች መሆናቸው እና ወንጀለኞቹ ዝርፊያውን የሚፈጽሙበት ፍጥነት ከፍተኛ መሆን እንዳሰበው ወንጀሉን መቆጣጣር እንዲቸገር አድርጎታል፡፡
ሆኖም በቀጠለው ጠንካራ ክትትል በዚህ ወር መጀመርያ የጀርመን፣ የኔዘርላንድ እና የፈረንሳይ የጸጥታ አካላት በጋራ ባደረጓቸው ዘመቻዎች 3 የከፍተኛ ወንጀል ቡድን አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋል ችለዋል፡፡
ባንኮቹን በመዝረፍ ራሳቸውን የተወሳሰበ አደጋ ውስጥ መጣል ያልፈለጉት ዘራፊዎች ከ2022 – 2024 ባሉት አመታት በሚሊየን ዩሮ የሚቆጠር ገንዘብ ከማሽኖቹ ዘርፈዋል፡፡
በዚህም ከአንድ ኤትኤም ላይ ከ100 ሺህ ዩሮ በላይ እንደሚዘርፉ ነው የተሰማው፡፡
ከዝርፍያው ጎን ለጎንም ማሽኖቹን ለማፈንዳት የሚጠቀሙባቸው ፈንጂዎች በመኖርያ እና በገበያ ህንጻዎች ላይ ያደረሱት ጉዳት 28.4 ሚሊየን ዩሮ ይገመታል፡፡
ይህን ተከትሎም የጀርመን ባንኮች 300 ሚሊየን ዩሮ በመመደብ የኤትኤሞቹን ደህንነት የሚያስጠበቁ አዳዲስ የደህንንት ማጠናከሪያ ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡