ሐሰተኛ የባንክ ቅርንጫፍ ቢሮ ከፍተው የሚያጭበረብሩት ሌቦች
አጭበርባሪዎቹ ለ10 ቀናት ህጋዊ ተቋም መስለው ቅርንጫፍ ከፍተው ሰዎችን ሲያታልሉ ነበር ተብሏል
ፖሊስ አጭበርባሪዎቹን እያደነ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን እስካሁን ተጠርጣሪዎቹ ስለመያዛቸው አልተገለጸም
ሐሰተኛ የባንክ ቅርንጫፍ ቢሮ ከፍተው የሚያጭበረብሩት ሌቦች
በዓለማችን በየዕለቱ በአታላዮች ተታለው ገንዘባቸውን የሚመነተፉ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
የማታለያ መንገዶቹ በየጊዜው መልካቸውን እየቀያየሩ የመጡ ሲሆን በሕንድ ደግሞ በይፋ በሀገሪቱ ዋነኛ መንግስታዊ ባንክ ስም ቅርንጫፍ ከፍተው ሲያጭበረብሩ ተገኝተዋል፡፡
በውድ ዋጋ ህንጻዎችን ተከራይተው፣ የቢሮ ቁሳቁስ አሟልተው ሲያጭበረብሩ የተገኙት እነዚህ ሰዎች ሰራተኞችን ለመቅጠር የእጅ መንሻ ሳይቀር ተቀብለዋል ተብሏል፡፡
ቻፖራ የተባለው መንደር በማዕከላዊ ሕንድ በሚገኘው ግዛት ስር ስትሆን በሕንድ መንግስት ባንክ ስም አዲስ ቅርንጫፍ በቅርቡ ተከፍቷል፡፡
ለዓመታት ያለ ስራ ከ16 ተቋማት ደመወዝ ስትቀበል የነበረችው አጭበርባሪ ተያዘች
ይህ ቅርንጫፍም ሰራተኞችን መቅጠር እንደሚፈልግ ማስታወቂያ ማውጣቱን ተከትሎ ነበር የ25 ዓመቱ ፒንቱ ዱርቬ የተባለው ሰው ለመቀጠር ያመለከተው፡፡
ፒንቱ ስራውን ለማግኘት 580 ሺህ ሩጲ ወጠይም 6 ሺህ 900 ዶላር ጉቦ እንዲከፍል በተጠየቀው መሰረት ይከፍላል፡፡
እሱን ጨምሮ ሌሎችም ሰዎች በዚህ አዲስ በተከፈተው የባንክ ቅርንጫፍ መቀጠራቸውን የሚናገረው ይህ ሰው ከባንኩ ዋናው ቅርንጫፍ ጋር በኔትወርክ እስከሚተሳሰር ድረስ የተቋሙን ህግ እና ሌሎች አሰራሮችን እያነበቡ እንዲቆዩ እንደተነገረውም ገልጿል፡፡
ይሁንና ቀስ በቀስ ከቅርንጫፍ ስራ አስኪያጁ ጋር የአካል ግንኙነት እየቀነሰ መጥቶ ጭራሽ የሚያናግራቸው ሰው እንዳጡም ተናግሯል፡፡
ቆይቶ ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቃቸውን ተከትሎ በተደረገው ምርመራ ጉዳዩ ማጭበርበር መሆኑ እንደተደረሰበት ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
አጭበርባሪዎቹ እስካሁን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሕንድ ሩጲ ወይም ከ14 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ከሰዎች አታለው መውሰዳቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን የተታለሉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል፡፡
የሕንድ መንግስት ባንክም ባወጣው መግለጫ ቻፖራ በተባለው መንደር አዲስ ቅርንጫፍ እንዳልከፈተ እና ደንበኞች እንዲጠነቀቁ አሳስቧል፡፡