የመረጃ መንታፊዎች የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትርን ጨምሮ ከ3500 በላይ የባንክ ሂሳቦች ላይ የሳይበር ጥቃት መፈጸማቸው ተገለጸ
ኢንቴሳ ሳንፓሎ የተሰኝ የሀገሪቱ ግዙፍ ባንክ የቀድሞ ሰራተኞች ናቸው ጥቃቱን እንዳደረሱ የተገለጸው
የድርጊቱ የመጀመሪያ ተጠርጣሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ማጣርያ እየተደረገበት ይገኛል
የቀሞ የጣሊያን ኢንቴሳ ሳንፖሎ ባንክ ሰራተኛ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ ባለስልጣናትን የባንክ ሂሳብ መረጃዎችን ይሰበስብ እንደነበር ተገለጸ፡፡
ፖለቲከኞች እና የህግ አስከባሪ መኮንኖችን ጨምሮ በአጠቃላይ 3500 የባንክ ሂሳቦች መረጃዎች በህገ-ወጥ መንገድ እና በተደጋጋሚ የሳይበር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ነው የተሰማው፡፡
የሀገሪቱ የመከላከያ ሚንስትር ጉየዶ ክሮሴቶ ፣ የቱሪዝም እና የአውሮፓ ጉዳዮች ዳንኤል ሳንታንቺ፣ የጸረ ማፍያ እና ጸረ ሽብር መከላከል ዳይሬክተር ጆቫኒ ሜሎ እንዲሁም በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የጣሊያን ተወካይ ሮቤርቶ ፊቶ የባንክ ሂሳባቸው በግለሰቡ ከተበረበሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ይህን ድርጊት እንደፈጸመ የተጠረጠረው የቀድሞ የጣሊያን ኢንቴሳ ሳንፖሎ ባንክ ሰራተኛ እንደሆነ የተነገረለት ቪኒሴንዞ ኮቪሎ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል፡፡
ፖሊስ በቤቱ ባደረገው ብርበራም ድርጊቱን መፈጸሙን የሚያመለካቱ የተለያዩ ስማርት ስልኮች፣ ታብሌቶች ፣ ሃርድ ዲስክ እና በርካታ ኮምፒውተሮችን መያዙን አስታውቋል፡፡
የሳይበር ጥቃቱ ከ6ሺህ ጊዜ በላይ መፈጸሙን ያስታወቀው ጉዳዩን እየተከታተለ የሚገኝው አቃቤ ህግ ባንኩ በየጊዜው በሚያደርገው አሰሳ ውስጥ ያልተለመደ የባንክ እንቅስቃሴ መመልከቱን ተከትሎ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ እንደተደረሰበት ነው የገለጸው፡፡
ከሳይበር ጥቃቱ ጀርባ ምን አይነት አላማ እንዳለ አላወኩም ያለው ፖሊስ ተጨማሪ ማጣርያዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡
የባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴ ከ2022 ጀምሮ ለሁለት አመታት ሲደረግ ከመቆየቱ ጋር በተያያዘ ጥቃቱን ፈጽሟል የተባለው የቀድሞ የባንኩ ሰራተኛ የሂሳብ እንቅሰቃሴዎችን አባዝቶ ስለመያዙ የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡
ቪኒሴንዞ ኮቪሎ በሁለት አመታት ውስጥ በ679 ቅርንጫፎች ላይ 3572 የባንክ ሂሳቦች ላይ የሳይበር ጥቃት ሲፈጽም የሂሳብ እንቅስቃሴ መረጃዎችን ከመውስድ ባለፈ ምንም አይነት የገንዘብ ዝውውር አለመፈጸሙ ታውቋል፡፡