ስለዞኑ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ህጋዊነት ጉዳይ የህግ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?
56 ብሄር ብሄረሰቦች የሚጉኙባቸው አምስት ክልሎች በ1987 ዓ.ም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት በአንድ ክልል እንዲደራጁ ከተደረገ ጀምሮ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ይበሉ እንጂ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች በስፋት ሲነሱ ቆይተዋል።
ይነሱ ከነበሩት የክልልነት ጥያቄዎች ጎልቶ የወጣው የሲዳማ ብሔር በክልልነት የመደራጀት ጥያቄም በህዳር ወር 2012 በተካሄደ ህዝበ ዉሳኔ (ሪፈረንደም) እልባት ማግኘቱ አይዘነጋም።
ከ1987 ጀምሮ ተመሳሳይ ጥያቄውን ሲያነሳ የነበረው የጉራጌ ህዝብ ባለፉት አራት አመታት በክልል ለመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ ግን እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
ሲዳማ ክልል የሆነበትን ተመሳሳይ ሂደት ተከትሎ ያቀረበው ጥያቄ አለመመለሱ ተቃውሞ ማስነሳቱን ቀጥሏል።
የክልልነት ጥያቄው ምላሽ እንዲሰጠው የጠየቁ ሰዎች ታስረዋል፤ የስራ ማቆም አድማ በማድረግም ተቃውሞዎች ተደርገዋል።
ዞኑ ለአንድ አመት ገደማ በኮማንድ ፖስት ስር መሆኑና ጥያቄው የሚፈታበት ግልጽ አቅጣጫ አለመቀመጡም ቀውስ መፍጠሩ ነው የሚነገረው።
አል አይን አማርኛም የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ህጋዊነት እስከምን ድረስ ነው? ህገመንግስቱን ተከትሎ ከቀረበስ መንግስት በፍጥነት ተገቢውን ምላሽ ለምን አልሰጠም ሲል የህግ ባለሙያዎችን እና የዞኑን የህዝብ ተወካዮች ጠይቋል።
የጉራጌ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ህጋዊ ነው?
የኢትዮጵያ ህገመንግስት የዜጎችን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ደንግጓል።
ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ በማንኛውም ጊዜ የክልልነት ጥያቄ በሚያነሳበት ወቅት ምላሽ የሚያገኝበት ሂደትን ህገመንግስቱ በግልጽ ማስቀመጡን የህግ ባለሙያው አቶ አሮን ደጎል ይናገራሉ።
የፌደራል መንግስቱ አባላትን በሚዘረዝረው የህገመንግስቱ አንቀፅ 47 ንኡስ አንቀጽ 2 የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የመመስረት መብት ከነቅድመ ሁኔታዎቹ ማስቀመጡንም ነው የሚያነሱት።
የክልልነት ጥያቄው በጠየቀው ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ተቀባይነት አግኝቶ ጥያቄው ለክልሉ ምክርቤት በጽሁፍ መቅረብ እንዳለበት መደንገጉንም ያክላሉ።
የክልሉ ምክር ቤትም ጥያቄው በደረሰው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ህዝበ ውሳኔ ማደራጀት እንደሚገባው ህገመንግስቱ አስቀምጧል።
በህዝበ ውሳኔው በክልልነት ለመደራጀት የጠየቀው አካል በአብላጫ ድምጽ ይሁንታን ከሰጠው አዲሱ ክልል እንደሚደራጅ በህገመንግስቱ መስፈሩን አቶ አሮን ያነሳሉ።
ህገመንግስቱ በአንቀጽ 47 ካሰፈራቸው በክልል የመደራጀት መብትና ሂደቶች ባሻገርም በአንቀጽ 39 ንኡስ አንቀጽ 3 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረስብና ህዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው” በሚል መደንገጉን የህግ ባለሙያው አቶ አምደገብርኤል አድማሱ ገልጸዋል።
የጉራጌ ህዝብ ያነሳው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ህገመንግስቱ ካስቀመጠውና የፌደሬሽን ምክርቤትን ለማቋቋም ከወጣው አዋጅ አንጻር ህጋዊነቱ እና ህገመንግስታዊ መብት መሆኑ አጠራጣሪ አለመሆኑንም የህግ ባለሙያው ያነሳሉ።
የዞኑ ምክርቤት ውሳኔ
በ1987 ዓ ም የደቡብ ክልልን ለመመስረት በሲዳማ ባህል አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ 33 የጉራጌ ሽማግሌዎች ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን የሚያወሱት የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ታረቀኝ ደግፌ፥ የጉራጌ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ለ28 አመታት ሲንከባለል መቆየቱን ይናገራሉ።
16 ወረዳዎች እና 8 የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረው የጉራጌ ዞን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ህዳር 17 ቀን 2011 በዞኑ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ሲጸድቅ እንደ አዲስ ጎልቶ መውጣቱንም ተናግረዋል።
ዞኑ የህዝቡን ፍላጎት ለመረዳት እስከታች ቀበሌ ድረስ ውይይት ማድረጉንና ህዝቡን የወከለው የዞኑ ምክርቤት በሙሉ ድምጽ ያጸደቀውን ውሳኔም ለክልሉ ምክር ቤት ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።
ይሁን እንጂ “የክልሉ ምክር ቤት በአንድ አመት ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ማደራጀት ሲገባው ዝምታን መርጧል፤ ለፌደሬሽን ምክር ቤትም የዞኑን ምክር ቤት ውሳኔ እና የህዝብ ፊርማን አሰባስበን አስገብተን እስካሁን ምላሽ አልተሰጠውም” ይላሉ የምክር ቤት አባሉ።
በነሃሴ ወር 2014 የጉራጌ ዞንን ከከምባታ፣ ስልጤ፣ ሃድያ፣ ሃላባና ሌሎች ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ጋር በክላስተር (ኩታገጠም) አዲስ ክልል ለማደራጀት የፌደራሉ መንግስት ሃሳብ ማቅረቡንና ሌሎቹ ሲደግፉት የጉራጌ ዞን 52 ለ40 በሆነ ድምጽ ውድቅ እንዳደረገውም ነው አቶ ታረቀኝ የሚያስታውሱት።
“የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በክላስተር በሚደራጀው ክልል እንደማይገባ ያሳለፈውን ውሳኔ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቢያሳውቅም ህገመንግስቱ የፈቀደልንን በህዝበ ውሳኔ በክልልነት የመደራጀት መብት አላስፈጸመም” ሲሉም የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ለማስከበር የተቋቋመውን የፌደሬሽን ምክር ቤትን ይከሳሉ።
የመንግስት ፖለቲካዊ ምላሽ
የፌደራሉ መንግስትም ህገመንግስታዊ መብትን ከማስከበር ይልቅ ፖለቲካዊ ፍላጎት የተጫነው ውሳኔ መስጠቱ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት መሆኑን የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ታረቀኝ ደግፌ ይናገራሉ።
“ምክንያታዊ፣ ህጋዊ እና ሁሉንም ተገቢ ሂደት የተከተለውን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ የክላስተር አደረጃጀቱን በግድ እንድንቀላቀል መታሰቡ አሳፋሪ ነው” ሲሉም ያክላሉ።
አንዳንድ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችም ህዝቡ በሙሉ ድምጽ ያጸደቀውን ውሳኔ ከማስፈጸም ይልቅ “ተቆጥቷል” የተባለውን የፌደራሉ መንግስት ለማስደሰት አቋማቸውን በአንዴ መለወጣቸውን የሚያስተዛዝብ ነው ብለውታል።
“አንድ ማህበረሰብ የሚጠቅመውን የሚወስነው ራሱ እንጂ አውቅልሃለሁ ተብሎ የሚጫንበትን እንደማይቀበለው መዘንጋት የለበትም፤ አሁንም የህዝብ ድምጽ ይደመጥ” ሲሉም ይጠይቃሉ አቶ ታረቀኝ።
ባለፉት አራት አመታት ለጉራጌ የክልልነት ጥያቄ የተሰጡት ምላሾች ህገመንግስቱን የተጻረሩና ፖለቲካዊ ፍላጎት የተንጸባረቀባቸው መሆኑን በማንሳትም፥ የፌደራሉ መንግስት አሳይቷል ያሉትን ህገወጥ ጣልቃገብነት ተቃውመዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤትም ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር ህዝበ ውሳኔ ማዘጋጀት ሲገባው “የካድሬ መልስ” መስጠቱን ገፍቶበታል ነው ያሉት።
ከጉራጌ ውጭ ያሉትም የክልልነት ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ የሚለው ስጋትም ለምላሹ መዳፈን አንዱ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ገልጸዋል።
ብልጽግና ፖርት ስለጉራጌ የክልል እንሁን ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ባይሰጥም የአደረጃጀት ጥያቄዎችን እንደማያበረታታ እና ፈተና እንደሆኑበት ይገልጻል።
የጉራጌ ዞን የሚገኝበት የደቡብ ክልል የገዥው ብልጽግና ፖርቲ ቅርጫፍ ኃላፊ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ከወር በፊት ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት የአደረጃጀት ጥያቄ ክልሉ የገጠመው ትልቅ ፈተና ነው።
ኃላፊው አዲስ ሀብት ሳይመነጭ መከፋፈሉ ህዝቡ ሊያገኝ የሚገባው የትምህርት፣ጤና እና የሌሎች መሰረተ ልማቶች አገልግሎትን ይገድባል የሚል ስጋት መኖሩን ገልጸዋል።
አዲሶቹ ክልሎች የበጀት እጥረት እንደገጠማቸው የገለጹት ኃላፊው አደረጃጀት ማብዛት አስፈላጊ አለመሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
ለጉራጌ የክልልነት ጥያቄ የደቡብ ክልል ምክር ቤትም ሆነ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምላሽ አልሰጡም።
የዞኑ ኮማንድ ፖስት ስር መሆን
የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ በህግ አግባብ አልፈታ ሲል ወልቂጤን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ለቀናት የዘለቁ የስራ ማቆም አድማዎች ተካሂደዋል።
ሱቆችና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን በመዝጋትም ህዝቡ ተቃውሞውን ማሰማቱን ቀጥሏል ይላሉ አቶ ታረቀኝ።
የዞኑ አመራሮች ግን ከህዝብ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች የስራ ማቆም አድማዎቹን የሚጠራቸው አካል አይታወቅም፤ ግጭት ቀስቃሽ ሃይሎች አካባቢውን የግጭት ቀጠና ሊያደርጉት አስበዋል የሚሉ አስተያየቶችን ሲሰጡ ተደምጧል።
የምክር ቤት አባሉ አቶ ታረቀኝ በበኩላቸው፥ “ተቃውሞው የመላው መብቱ የተነፈፈው የጉራጌ ህዝብ ነው፤ የህዝቡን ጥያቄና ተቃውሞ ለማፈንም የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን ቀጥለዋል” ብለው ያምናሉ።
“ኮማንድ ፖስቱ ህዝብን ስጋት ውስጥ በመጣል ሳይፈልግ በክላስተር አማራጩ እንዲጠቃለል ታስቦ የተጫነ እንጂ አካባቢው የደህንነት ስጋር ያለበት ሆኖ አይደለም” የሚል አስተያየታቸውንም ያክላሉ።
የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን በጉልህ እንዲሰማ ያደረጉ ሰዎችን የማሰርና የማንገላታቱ ጉዳይ እራሳቸው ጭምር ያለመከሰስ መብታቸውን ተነፍገው ከአንድ ወር በላይ መታሰራችውን በአብነት በማንሳት ጠቁመዋል።
ኮማንድ ፖስቱ የዜጎችን የሰብአዊ መብት እና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት እየገደበ ነው ብለዋል።
ቀጣይ እጣ ፈንታው እና ስጋቱ
የጉራጌ ዞን በክላስተር አደረጃጀቱ አልካተትም በማለቱ ስያሜ እና አደረጃጀቱን በሚቀይረው የደቡብ ክልል ውስጥ ይቆይ የሚሉ ምክረሃሳቦች እየቀረቡ መሆኑ ተነግሯል።
አቶ ታረቀኝ ግን የ28 አመታት የህዝቡ ህጋዊ ጥያቄ ምላሽ የማግኘቱ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው ባይ ናቸው።
የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የፌደራሊዝሙ ትሩፋት አድርጎ የሚያቀርበው መንግስት፥ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን በሌላ መነጽር ማየት ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስም ህገመንግስታዊ መሰረት ያለው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ይጠይቃሉ።
ያነጋገርናቸው የህግ ባለሙያዎችም መንግስት ለህገመንግስታዊ ጥያቄዎች የማያሻማና ህጋዊ መልስ መስጠት እንዳለበት ያምናሉ።
ህገመንግስቱ ለብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሰጠውን መብት ለአንዱ መስጠትና ለሌላው መንፈግም ከህግ ጥሰትነቱ ባሻገር ለሌላ ትርጉምም ሊያጋልጥ ስለሚችል ህጉን ተከትሎ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።
መንግስት በሌላ እስካልተካው ድረስ ህገመንግስቱን የማክበርና የማስከበር ሃላፊነቱንም ሊዘነጋው እንደማይገባ አሳስበዋል።
በቅርቡ በዞኑ በውሃ እጥረት ምክንያት በተነሳ ተቃውሞ የጸጥታ አካላት በወሰዱት ያልተመጣጠነ እርምጃ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል።