ከክልሉ የተነጠሉ አዲስ አደረጃጀቶች የገጠማቸው የበጀት እጥረት “መሰረታዊ አገልግሎቶችን” እንዳናቀርብ አድርጎናል ማለታቸው ይታወሳል
የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመባል የሚታወቀው ክልል ከ2010 ዓ.ም. መባቻ ብቻ 10 የሚሆኑ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ አንስተውበታል።
በ1980ዎቹ አጋማሽ አምስት ክልሎች በአንድ ላይ ተሰባስበው የመሰረቱት ክልል “የመዋቅር ጥያቄ የፈነዳበት” ክልል በመባልም ይታወቃል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ሁለት ክልሎች የተነጠሉት ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ መቆየቱን ወይም መነጠሉን የሚወስነውን ምርጫ ከቀናት በኋላ ያደርጋል። እንደ ጉራጌ ያሉ ዞኖች ደግሞ የአደረጃጀት ጥያቄያቸውን እንደያዙ አሉ።
ባለፉት ዓመታት የክልል ጥያቄዎች ፍትኃዊ የሀብትና የስልጣን ክፍፍልን በመሻት እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ መብትን በመጠቀም ተካሂደዋል። በደቡብ ክልል የተነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለክልሉ ትኩሳትና መጻኢ-እድል ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል።
በተለይም “አንዷን ዳቦ ለአራት መካፈል” ጾም የሚያድረውን እንዳያበዛ በመንግስት ተሰግቷል።
የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፓለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል “የአደረጃጀት ጥያቄ” ክልሉ የገጠመው ትልቁ ፈተና ነው ይላሉ።
አዲስ ሀብት ሳይመነጭ መከፋፈሉ ማህበረሰቡ ማግኘት ያለበት እንደ ትምህርት፣ ጤናና ውሃ የመሰሉ መሰረተ-ልማቶች እንዲገደቡ ያደርጋል በማለት ስጋቱን ገልጸዋል።
ኃላፊው ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት በተለይም በጀት እንደ ነዳጅ፣ ውሎ-አበልና ደመወዝ ለመሰሉ አስተዳደራዊ ወጪዎች ብቻ ማዋልን አስገድዷል።
“አዲስ የሚጨመር ሀብት ሳይኖር የሚከፋፈለው ሀብት አንድ ነው። የአስተዳደር ወጪ ለሁለት ይከፈላል። ስለዚህ የሀብት ብክነትን ይጨምራል ማለት ነው። ለማህበረሰቡ መሰረታዊ አገልግሎቶች ለትምህርት፣ ለጤና ውሃ ይውል የነበረው ለአስተዳደራዊ ወጪ ይወጣል ማለት ነው። በነዳጅ፣ በውሎ-አበል፣ በደሞዝ ብቻ ይቀራል” ብለዋል።
ደቡብ ክልል (ዳግም በመደራጀት ላይ ያለ) ሲዳማ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዲሁም በቅርቡ ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቀው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተነጥለውታል።
በክልሉ “አደረጃጀት ያለአግባብ ግንዛቤ ውስጥ ገብቷል” የሚሉት ስንታየሁ ወ/ሚካኤል፤ ጥያቄው ሲነሳ እውነተኛ ጥቅም ለህብረተሰቡ ይሰጣል ወይ የሚለው እይታ ላይ ጉድለት አለ ብለዋል። “የተመጠነ” አደረጃጀትን የሚወተውቱት ኃላፊው፤ ይህ ባለመሆኑ የበጀት እጥረትና ሌሎች ችግሮችም ገጥመዋል ይላሉ።
ኃላፊው አዲሶቹ ክልሎች የበጀት እጥረት እንደገጠማቸውም ተናግረዋል።
አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ የበጀት ውስንነት ሰራተኞችን ለመቅጠር እንቅፋት እንደሆነበት አሳውቋል።
የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው “[በክልል ጥያቄ] ሀብት የሚያፍስ የሚመስለው ብዙ ነው። በዚህም አግባብ ቅስቀሳ ይደረጋል። ከጠቀመም መንግስት እርከን ላይ ላለው ነው [የሚጠቅመው]። አደረጃጀት ማብዛት ለሰፊው ህዝብ የሚጠቅም አይደለም” በማለት የክልሉን ፈተናና የበጀት ክፍፍል ገልጸዋል።
“በአንድ አስተዳደራዊ ወጪ ይሸፈን የነበረ ግልጋሎት አሁን ወደ አራት ክልሎች ይሄዳል” በማለት የገጠማቸውን የሀብት ውስንነት የሚናገሩት ስንታየሁ ወ/ሚካኤል፤ “ዞሮ ዞሮ ተጽዕኖው ለራስ ነው” ይላሉ።
የተመጠነና ደረጃ የወጣለት አደረጃጀት መቀየስ እንደሚያስፈልግ፤ ይህም የፓርቲያቸው አቋም መሆኑን ጠቁመዋል። “ብልጽግና በየቦታው የሚፈለፈል አደረጃጀት እንዲኖር ፍላጎት የለውም። የተመጠነና የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽል እንዲሆን ነው። ከዚህ በኋላ የሚደራጁ ክልሎች እነዚህን ሁኔታዎች ታሳቢ ያደርጋሉ። ደረጃ ያለው፣ የተመጠነ የሰው ኃይል፣ ከፍተኛ የአስተዳደራዊ ወጪ በማያመጣ መልኩ ይሆናል” ብለዋል።
ክልሉ የገጠመውን ችግር ለመፍታት ሀብቱን ማጥናት ላይ አይኑን ጥሏል። ነባሩን ደቡብ ክልል በቀሩት አደረጃጀቶች ዳግም የሚያደራጀውና የደቡብ ኢትዮጵያን ክልል የሚመሰርተው ልዩ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ክልሉ ያለውን አቅም ማወቅ ላይ ይሰራልም ተብሏል። ሀብቱን በማጥናትና እንዴት መጠቀም እንደሚችል ትኩረት እንደተሰጠው የፖለቲካ ዘርፈር ኃላፊው ጠቅሰዋል።
“ምን አለን የሚለው አጠቃላይ በሁለቱም [ነባሩ ደቡብ ክልልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል] ያሉን ጸጋዎች ይለያሉ። እነዚህን ጸጋዎች በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ የሚያውል እቅድ ይወጣል። ለሁለቱም ክልሎች የ10 ዓመት ስልታዊ እድዶች የዘጋጃሉ። [እቅዱ] አቅምን መነሻ ያደርጋል። ይህን ተመስርቶ ሀብት የማሰባሰብና በውስጥ አቅም አካባቢን የማልማት ስራ ለመስራት አስበናል” ሲሉ አብራርተዋል።
ከነባሩ የደቡብ ክልሉ በመውጣት ሌሎች ክልሎች ሲመሰረቱ የክልሉ በጀት እየቀነሰ ሄዷል፡፡
ደቡብ ክልል በ2013 ዓ.ም. 38 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት ነበር። በ2014 ዓ.ም. 32 ነጥብ 37 ቢሊዮን ብር፤ በተያዘው የ2015 በጀት ዓ.ም. ደግሞ 26 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል።