ነባሩ የደቡብ ክልል ሰሙን ቀይሮ አዲስ ክልል ሆኖ ሊደራጅ ነው
የጉራጌ የክልል ጥያቄ ዳግም ራሱን ከሚያደራጀው ክልል ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ተብሏል
ነባሩ የደቡብ ክልል “የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል” በሚል ስያሜ አዲስ ክልል ሆኖ እንደሚመሰረት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫት ጽ/ቤት ገልጿል
የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ይባል የነበረው ክልል ከስያሜው ጀምሮ መቀመጫውን፣ ሰንደቅ-ዓላማውንና አደረጃጀቱን ሊቀይር ነው።
ክልሉ በ56 ብሄረሰቦች ተደራጅቶ መቀመጫቸውን ሀዋሳ ያደረገ ሲሆን፤ ባለበት መቀጠል የማያስችለው "ነባራዊ ሁኔታ" መፈጠሩን ተናግሯል።
በክልሉ ውስጥ የነበሩ በርካታ ብሄረሰቦች በቡድን እና በተናጠል የየራሳቸውን ክልል መስርተዋል፡፡ ቀድሞ ክልል መሆን ቻለው ሲዳማ ዞን ነበር፡፡
ሲዳማ ዞንን ጨምሮ ሁለት ክልሎች የተነጠሉትና ሦስተኛው በመንገድ ላይ በሆነው ደቡብ ክልል ስድስት መዋቅሮችና 10 ብሄር ብሄረሰቦች ብቻ ቀርተዋል።
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫት ጽ/ቤት የፓለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት በክልሉ የተፈጠረው እውነታ እንደገና ገጽታውን ማስተካከል አስገድዷል።
"አሁን የሚቀረው ክልል ህገ-መንግስቱን እንዲያሻሻል፣ ስያሜውን እንዲቀይር፣ ማዕከሉን እንዲቀይር የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጥሯል" ብለዋል።
ለነባራዊ ሁኔታው ማሳያ የሚጠቅሱት ኃላፊው "ለምሳሌ ባንዲራችንን ብንመለከት በፊት በነበረው አርብቶ-አደር፣ አርሶ-አደሩም በአንድ ላይ ይኖሩ እንደነበር የሚያሳይ ነው። አሁን አርብቶ አደር ክፍል አይኖርም ማለት ነዉ። ይለያል። ብዙ ነገሩ ይለያል። ስለዚህ የስያሜም መቀየር ጉዳይ ግድ ሆኗል ማለት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
“ለአዲሱ ክልል” ከቀረቡ ስያሜዎች መካከል ክልል ሰባት፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ሸዋ ክልል እንዲሁም ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚሉ አማራጮች ይገኙበታል። ክልሉ ታሪኩን፣ መልከኣ-ምድራዊ አቀማመጡን፣ ህዝቡንና ሀብቱን ተመርኩዞ በጊዜያዊነትም ቢሆን “ማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክልል” የሚለውን ስያሜ ይዞ ለመደራጀት እየተንቀሳቀሰ ነው።
የህገ-መንግስት ማሻሻያ በማድረግ ክልሉን ዳግም የመመስረት እንቅስቃሴ በሦስት ምዕራፎች ተከፍሎ እየተካሄደ መሆኑን ሰምተናል።
የአደረጃጀት ለውጥ ይኖር እንደሆነ የጠየቅናቸው ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ጥናትን መሰረት ያደረገ ለውጥ እንደሚኖር ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ደቡብ ክልል "ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል" በሚል ለመመስረት ህዝበ-ውሳኔ እንጂ የህገ-መንግስት ማሻሻያ መደረግ የለበትም የሚሉ ወገኖች አሉ። በተለይም የጉራጌን የክልል ልሁን ጥያቄን በማንሳት "በአዲሱ ክልል" ለመደራጀት የህዝብ ይሁንታ ያስፈልጋል ይላሉ።
የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ የክልል መስረታው “እድሳት” በመሆኑ ህዝበ-ውሳኔ አያስፈልግም ባይ ናቸው።
"የፌዴሬሽን ም/ቤት ግልጽ ውሳኔዎችን ነው የወሰነው። [ከሚመሰረተው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውጭ] ቀሪዎቹ ባሉበት ራሳቸውን "ሪብራንድ" አድርገው ይቀጥሉ ብሏል።" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የፌዴሬሽን ም/ቤት ጉዳዩ የህዝበ-ውሳኔ ጥያቄ የሚያስነሳ አይደለም ብሏል።
የም/ቤቱ የህዝብ ግንኙነተ ኃላፊ ተፈረ በዳዳ ለአል ዐይን አማርኛ የጉራጌ የክልል ልሁን ጥያቄ በም/ቤቱ ምላሽ ስላገኘ፤ ዳግም ራሱን ከሚያደራጀው ክልል ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“የጉራጌ ጥያቄ ቀርቦ፤ የጉራጌ ህዝብ ተወያይቶበት በፌዴሬሽን ም/ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶበታል። የተሰጠው ውሳኔ አሁን እንደ አዲስ የሚነሳበት ምክንያት የለም። ለህዝብ የተግባቦትና የማሳመን ስራ ተሰርቷል። ጥያቄ ጠየቁ ጥያቄያቸው ምላሽ አግኝቷል። ምላሽ ሲባል አዎ ወይም አይሆንም ሊሆን ይችላል። ምላሽ አግኝቶ ያደረ ጥያቄ ነው። ስለዚህ ምላሽ ያገኘን ጥያቄ ስም ከመቀየር፣ “ከሪብራንድ” ጋር የሚያያዝ ነገር የለም” ብለዋል።
ተፈረ በዳዳ ለደቡብ ክልል እንቅስቀሴ ምርጫ እንደማያስፈልገውም ተናግረዋል። ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ስሜን እቀይራለሁ ካለ ኃላፊነቱ የራሱ ነው፤ የሚል ማሳያ ያቀረቡት ኃላፊው ህዝበ-ውሳኔ ጋር የሚደርስ ነገር የለም ሲሉ፤ የክልሉ መብት እንደሆነ ተናግረዋል።
የፌደሬሽን ምክርቤት የጉራጌ ዞን በነባሩ ደቡብ ክልል ከቀሩት ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ጋር ሆኖ አዲስ ክልል እንዲደራጅ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፤ይህም በጉራጌ ዞን ለተነሳው ተቃውሞ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።
“የደቡብ ክልል ቀሪ አደረጃጀቶች አንድ ላይ እንዲቀጥሉ ነው የተወሰነው። “ሪብራንድ” ማድረግ ይችላል። ከፌደሬሽን ም/ቤት ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም። ምክንያቱም “ሪብራንድ” ማድረግ የክልሉ ስልጣን ስለሆነ” ብለዋል።
ነባሩ የደቡብ ክልል ህገ-መንግስቱን የማሻሻል መብት እንዳለው የጠቀሱት ኃላፊው፤ የፌዴራሉን ህገ-መንግስት እስካልተቃረነ ወይም እስካልተጣረሰ ድረስ ይችላል ብለዋል።
በህገ-መንግስት ማሻሻያው “መሰረታዊ” የተባሉ ድንጋጌዎች እንደሚሻሻሉ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ለአል ዐይን ተናግረዋል። የክልሉ ስያሜ፣ ሰንደቅ-አለማ፣ የክልሉ ዋና ከተማ (ማዕከል) እንዲሁም የክልሉ አደረጃጀት ለውጥ ይደረግባቸዋል ብለዋል።
ደቡብ ክልል አደረጃጀቱን ዳግም ሲደራጅ፤ የዞን፣ የወረዳና የልዩ ወረዳ መዋቅሮች እንደሚታዩም ተጠቁሟል።
በመሆኑም በነባሩ ደቡብ ክልል ስር የነበሩ 10 ብሄር ብሄረሰቦችና ስድስት መዋቅሮ ማለትም ጉራጌ፣ ሀድያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮና ሀላቦ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳ በአዲሱ ክልል “ጥናትን መሰረት አድርጎ” ዳግም ይደራጃሉ ተብሏል።
የአዲሱ ክልል ዋና መቀመጫ እነማን ለመሆን ታጭተዋል ስንል ለፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው ጥያቄ ብናነሳም፤ አሁን ላይ እገሌ ማለት አይቻልም ብለዋል።
የአዲሱ ክልል የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የክልል ምስረታ ጉባኤውም እስካሁን ቀን እንዳልተቆረተለት ማወቅ ችለናል።ክልሉ መልኩን በመለወጥ እንቅስቃሴው አሁን ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ነኝ ያለ ሲሆን፤ በሦስተኛው ምዕራፍ ስልጣንና ሀብት ማጋራትን የመሳሰሉ ጉዳዮችን እሰራለሁ ብሏል።