ሲዳማን ሞዴል ክልል ሊሆን በሚችል መልኩ ለማደራጀት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
“በሲዳማ ክልል የሚደራጁ ዞኖች የራሳቸው ም/ቤት አይኖራቸውም”
ለረዥም ዘመናት የቆየው የሲዳማ ህዝብ የክልልነት ጥያቄ እንቆቅልሽ ሲፈታ ፣ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲዳማ በክልል ለመደራጀት ህዝበ ዉሳኔ ያካሔደበት ቀን ነው፡፡ በኢትዮጵያ አዲስ ክልል ለመመስረት ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሔደው በዚህ ህዝበ ዉሳኔ በደቡብ ክልል ዉስጥ ይገኝ የነበረው የቀድሞው ዞን ከ 98% በላይ ድምጽ በማግኘት 10ኛው ክልል መሆን ችሏል፡፡
ከደቡብ ክልል ጋር የመለያየት ሂደቶች አጠናቅቆ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ሲዳማ ክልል ከነባሩ የደቡብ ክልል ስልጣን ተረከበ፡፡
በመቀጠልም ከወር በፊት ሰኔ 27 ቀን 2012ዓ.ም. የሲዳማ ክልል በይፋ ተመሰረተ፡፡
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በይፋ ሲመሰረት አቶ ደስታ ሌዳሞ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተመርጠዋል። 190 አባላት ያሉት የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ተመስርቶ የክልሉን ሕገ መንግሥት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። አቶ ሰለሞን ላሌ የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነዋል።
የክልሉ መዋቅር እና ዉስጣዊ አደረጃጀት
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት በደቡብ ክልል ምክር ቤት ሲዳማን ይወክሉ የነበሩ አባላትን ፣ የቀድሞውን የሲዳማ ዞን ምክር ቤት አባላት እንዲሁም ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ም/ቤት የተካተቱ 30 አባላትን በማጠቃለል በ190 አባላት ተዋቅሯል፡፡ ከአባላቱ 70ው (37%) ሴቶች ናቸው፡፡
ከቢሮ አወቃቀር ጋር በተያያዘ በካቢኔ የሚመሩ 18 ቢሮዎች ተደራጅተው ስራ መጀመራቸውን የሲዳማ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ፊሊጶስ ናሆም ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
ቀጣዩ ጥያቄ ዉስጣዊ አደረጃጀትን የተመለከተ ነው፡፡ ከዞንና ከወረዳ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዴት ይመለሳሉ የሚለውን በተመለከተ የሲዳማ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በሰጡት ማብራሪያ ጥያቄዎቹ በሳይንሳዊ ጥናት መፍትሔ እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡
በክልል ደረጃ ገና ያላለቁ አደረጃጀቶች መኖራቸውን ያነሱት አቶ አብርሃም ክልላዊ አደረጃጀቶች ሲያልቁ የዞንና የወረዳ አደረጃጀቶች ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
አቶ አብርሃም ማርሻሎ - የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ
በቀጥታ ለክልሉ ተጠሪ የሚሆነውን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርን ሳይጨምር ፣ ከዚህ ቀደም ፣ ክልሉን በ4 ዞኖች ለማደራጀት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚካሔዱ ነው የተገለጸው፡፡ ይሁን እንጂ የዞን አደረጃጀቱ በደቡብ ክልል ባለው አይነት ወይም እንደቀድሞው የሲዳማ ዞን እንደማይሆን አቶ አብርሃም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሲዳማ በዞን ደረጃ በነበረበት ወቅት በርካታ የሰው ኃይል እና የራሱ ምክር ቤት ያለው ሲሆን አሁን በክልሉ ስር አዲስ የሚመሰረቱ ዞኖች ግን በጣም ዉስን የሰው ኃይል ይዘው የራሳቸው ምክር ቤት ሳይኖራቸው የሚደራጁ ናቸው፡፡
የዞን ኃላፊነት ክልልን ከወረዳዎች ጋር ማስተሳሰር ብቻ ነው፡፡ ዞናዊ አደረጃጀቱ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የማስተባበር ሚና ብቻ እንደሚኖረው ነው አቶ አብርሃም የተናገሩት፡፡ በመሆኑም ዞን የሚደራጀው በጣም በጥቂት የሰው ኃይል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ከዞን አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ከህዝቡ ጋር ዉይይት የተደረገ ሲሆን ዉይይቱ እንደሚቀጥልም አንስተዋል፡፡ በተመሳሳይ የዞን መቀመጫዎች የት እንደሚሆኑም ከህዝቡ ጋር በመመካከር ዉሳኔ ይሰጣል ያሉት አቶ አብርሃም ዋናው ነገር አደረጃጀቶች ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ብቻ ታስበው የሚመሰረቱ መሆናቸው ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል፡፡ የዞን መቀመጫ የትም ይሁን የት ፣ አደረጃጀቱ እጅግ የሳሳ እና ዉስን የሰው ኃይል ብቻ ያለው በመሆኑ የዞን መቀመጫ የሚሆን ከተማ የተለየ የሚያገኘው ጥቅም እንደማይኖር ጠቁመዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ሰንደቅ ዓላማ
ከወረዳ መዋቅር ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት በሲዳማ ክልል 36 ወረዳዎች (6ቱ የከተማ አስተዳደሮች) ይገኛሉ፡፡ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ 8 ክፍለ ከተሞችም እያንዳንዳቸው እንደወረዳ ነው የሚቆጠሩት፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ የወረዳ ጥያቄዎች አሁንም በመነሳት ላይ ናቸው፡፡
እስካሁን የወረዳ ጥያቄዎች በስፋት ምላሽ እንደተሰጣቸው የተናገሩት የሲዳማ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ አዲስ የሚነሱትም ቢሆኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ከተመለሱ በኋላ በመመካከር ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እንጂ ወረዳ ለመፍጠር ተብሎ የሚፈጠር ወረዳ የለም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ቀጣይ ፈተናዎች
የሲዳማ ክልል አስተዳደር በይፋ በተመሰረተበት ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባደረጉት ንግግር የአዲሱ ክልል ቀጣይ ፈተናዎች ብለው ከጠቀሷቸው ነጥቦች መካከል ከጎሳ ጋር የተያያዙ እና የስራ አጥነት ጉዳዮች በዋናነት ይነሳሉ፡፡
አቶ ደስታ ሌዳሞ - የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
ከጎሳ ጋር ተያይዘው የሚነሱት ከስልጣን እና ከዉስጣዊ አደረጃጀት ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ክልሉ በአሁኑ ወቅት የሰው ኃይል በማሟላት ላይ የሚገኝ ሲሆን ለተለያዩ ኃላፊነቶች የሚሰየሙ የሥራ ኃላፊዎችም ይሁኑ ሌሎች ሰራተኞች እውቀትን ብቻ ባማከለ መልኩ ለቦታው የሚመጥኑ እና ህዝቡን በአግባቡ የሚያገለግሉ መሆናቸው እየተመዘነ እንደሚመረጡ አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡
ሲዳማን ለሌሎች ሞዴል ክልል ሊሆን በሚችል መልኩ ለማደራጀት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ያነሱት አቶ አብርሃም በሲዳማ ዉስጥ የሚገኙ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም እኩል የሚስተናገዱበት እና የሚጠቀሙበት ክልል ለመፍጠር ትኩረት እንደተሰጠ ተናግረዋል፡፡
“የሲዳማ ህዝብ አቃፊ እንጂ ገፊ አይደለም” ያሉት አቶ አብርሃም “ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ጉዳዮችም ቢሆኑ በታቀደ መልኩ ዓላማ ባነገቡ ግለሰቦች ታቅዶ የተፈጸመ እንጂ በሲዳማ ህዝብ ታቅዶ የተፈጸመ አይደለም” ብለዋል፡፡
አቶ ደስታ ሌዳሞም ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር መሰል ሀሳብ አንጸባርቀዋል፡፡ “ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የዉጭ ዜጎችም በሲዳማ ክልል መጥተው በነጻነት መኖር ይችላሉ” ያሉት አቶ ደስታ ምንም እንኳን ህዝባዊ መሰረት ያለው ባይሆንም ክልል ለመሆን በነበረው ሂደት ስለተፈጠሩ ችግሮች እና በዚህም የተጎዱ አካላትን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
አሁን ላይ የክልሉ የጸጥታ መዋቅርም ሆነ አጠቃላይ አደረጃጀት ሁሉም ሊጠቀሙና በእኩልነት ሊስተናገዱ በሚችሉበት መልኩ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች ሁሉ የወጣቱ የስራ እድል ጥያቄ የሲዳማም ቀጣይ ሁነኛ ፈተና ነው፡፡ አቶ አብርሃም ማርሻሎ የሲዳማ ወጣት ጥያቄዎች የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መሆናቸውን ጠቅሰው የፖለቲካ ጥያቄው በአብዛኛው ምላሽ ቢያገኝም የኢኮኖሚው ግን ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
“በስራ አጥነት ዉስጥ የሚገኝ ወጣት ለአፍራሽ ሃይሎች መጠቀሚያ መሆኑን ይቀጥላል” ያሉት አቶ አብርሃም “የስራ እድል ፈጠራ ላይ አቅደን እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡ ለስራ እድል ፈጠራም ይሁን ለሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በተደራጀ መልኩ ሌት ተቀን እየተሰራ እንደሚገኝም አውስተዋል፡፡
አጠቃላይ በክልሉ ለማስፈን የታቀዱ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስርዓቶችን ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች በአንድነት እንዲተባበሩም ተጠይቋል፡፡