በውጤቱ መሰረት የኮንታ ልዩ ወረዳን ጨምሮ የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮ እና የሸካ ዞኖች 11ኛው የፌዴሬሽኑ ክልል ሆነው የሚዋቀሩ ይሆናል
በኢትዮጵያ 11ኛውን ክልል ለመመስረት በአምስት ዞኖችና በአንድ ልዩ ወረዳ የተካሄደው ሕዝበ ድምጽ ዛሬ ይፋ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ውጤቱን አስመልከተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው ይፋ በሆነው የህዝበ ውሳኔው ውጤት መሰረት የኮንታ ልዩ ወረዳን ጨምሮ የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮ እና የሸካ ዞኖች 11ኛው የፌዴሬሽኑ ክልል ሆነው የሚዋቀሩ ይሆናል፡፡
ህዝበ ውሳኔው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በካፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ አስተዳደሮች ባቋቋማቸው 1 ሺህ 613 ምርጫ ጣቢያዎች በ22 ምርጫ ክልሎች ነው ባሳለፍነው መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ/ም የተካሄደው።
ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ በተደረገበት እና 1 ነጥብ 34 ሚሊዮን ሰዎች ካርድ በወሰዱበት በዚህ ህዝበ ውሳኔ 1 ነጥብ 29 ሚሊዮን መራጮች ድምጽ ሰጥተዋል፤ ከአራት ሺህ በላይ ሰዎች በምርጫ አስፈጻሚነት ተሳትፈዋል እንደ ቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ገለጻ፡፡
በዚህም አምስቱ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳ ራሳቸውን ችለው ክልል የሚሆኑ ይሆናል፡፡ ይህ “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” 11ኛው የፌዴሬሽኑ አካል ሆኖ መዋቀሩን የሚያመለክት ነው፡፡
ከ2 ዓመታት በፊት ሲዳማ 10ኛው የፌዴሬሽኑ ክልል ሆኖ መዋቀሩ የሚታወስ ነው፡፡
የአሁኑ ሕዝበ ውሳኔም የከፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ አስተዳደሮች በአንድ ክልል ስር ለመዋቀር መስማማታቸውን ተከትሎ የተካሄደ ነው፡፡
በሕዝበ ውሳኔ መሰረትም “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” ሕገ መንግስት እየተዘጋጀለት መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ፕሮጄክት ጽ/ቤት ከአሁን ቀደም ለአል ዐይን አማርኛ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ ምትኩ በድሩ (ኢ/ር)፣ ከወራት በፊት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ አዲስ ይዋቀራል ተብሎ ለሚጠበቀው ክልል የሰነድ ስራዎች እየተዘጁለት መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
የክልል ስያሜ ፣ ሰንደቅ ዓላማ ፣ የሥራ ቋንቋና ሌሎችም ጉዳዮች የሚካተቱበት ሕገ መንግስት እየተዘጋጀ እንደሆነም ተገልጿል፡