ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የሳዑዲ አረቢያውን አል-ናስር የእግር ኳስ ክለብን ተቀላቅሏል
ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳስ ታሪክ ውዱ ተከፋይ ያደረገውን ስምምነት ከሳዑዲው ክለብ ጋር ተፈራርሟል።
የአምስት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ከተለያየ በኋላ ያለ ክለብ የቆየ ሲሆን፤ በመጨረሻም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማቅናቱ ትናንተ ምሽት ተረጋግጧል።
- ክርስትያኖ ሮናልዶና ማንችስተር ዩናይትድ በስምምነት መለያየታቸውን ክለቡ ይፋ አደረገ
- ፓርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ "ተከድቻለሁ" አለ
በዚህም ሮናልዶ ከሳዑዲ አረቢያው አል-ናስር ጋር ለሁለት ዓመት የሚያቆየውን ውል መፈራረሙም ይፋ ሆኗል።
ሮናዶ በአል ናስር ቆይታው በዓመት 170 ሚሊዮን ፓውንድ ይከፈለዋል የተባለ ሲሆን፤ ይህም በእግር ኳስ ታሪክ የዓለማችን ውዱ ተከፋይ እንደሚያደርገውም ተመላክቷል።
የአምስት ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው የ37 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ፊርማውን ካኖረ በኋላ በሰጠው አስተያየት፤ "በተለየ ሊግ እና ሀገር ውስጥ አዲስ ልምድ ለማግኘት ጓጉቻለሁ” ብሏል።
“በአውሮፓ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ለማሸነፍ የምመኛቸውን ሁሉ ማሳካት በመቻሌ እድለኛ ነኝ” ያለው ሮናልዶ፤ “አሁን ደግሞ ልምዴን በእሲያ ሊግ ውስጥ የማካፍልብት ጊዜ ነው” ሲልም ተናግሯል።
የሳዑዲ ሊግ የ9 ጊዜ ሻምፒዮናው አለ ናስር በበኩሉ የፊርማ ስነ ስርዓቱን ታሪክ እየተሰራ ነው ሲል ገልጾታል።
ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ማንችስተር ዩናይትድ በስምምነት መለያየታቸውን ክለቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የ37 አመቱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ በቶክ ቲቪ ባደረገው ሰፊ ቃለ ምልልስ ከዩናይትድ እየተገፋ እንደሆነ እንደሚሰማው፣ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግን እንደማያከብር እና የግላዘር ቤተሰብ ለክለቡ ምንም ደንታ እንደሌለው መናገሩ አይዘነጋም።
ሮናልዶ በማንችስተር ዩናይትድ በቆየባቸው ጊዜያት በ346 ጨዋታዎች 145 ጎሎችን በማስቆጠር ከክለቡ ታላላቅ ተጫዋቾች በቀደሚነት የሚመደብ ነው።