“በዩናይትድ ተከድቻለሁ” ያለው ሮናልዶ ከቀያዮቹ ሰይጣኖች ጋር ክፉኛ እያነታረከው ነው
ማንቸስተር ዩናይትድ በክርስቲያኖ ሮናልዶ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።
ፖርቹጋላዊው ኮከብ በቶክ ቲቪ ለፒርስ ሞርጋን የሰጠው ቃለመጠይቅ፥ ከክለቡ ጋር ክፉኛ አቃርኖታል።
ክለቡ ባወጣው መግለጫም በ37 አመቱ ተጫዋች ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ገልጿል። የመጨረሻውን ውሳኔም ሂደቱ ሲጠናቀቅ አሳውቃለው ያለው ዩናይትድ፥ ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስድ ከመግለፅ ተቆጥቧል።
ተንታኞች ግን በዩናይትድ ተከድቻለሁ ያለው ሮናልዶ ከቀያዮቹ ሰይጣኖች ጋር መለያየቱ እንደማይቀር እየገለፁ ነው። ክለቡ ኮንትራቱን ከማቋረጥ እስከ ህጋዊ እርምጃ ድረስጰበሮናልዶ ላይ ሊወስድ ይችላል።
በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ተከፋዩ ሮናልዶ የገንዘብ ቅጣትም ሊጠብቀው እንደሚችል የሚገልፁ አሉ። ክለቡ ግን ሂደቱ ሲጠናቀቅ አሳውቃለሁ ከማለት ውጭ ፍንጭ አልሰጠም።
ዩናይትድ በሮናልዶ ክብር ከተነፈገው ከአሰልጣኙ ኤሪክ ቴንሀግ እና ከጠቅላላ ስታፉ ጎን እንደሚቆም ነው ያስታወቀው፤ በክለቡ ክብር እንደማይደራደርም ገልጿል።
- ፓርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ "ተከድቻለሁ" አለ
- ክርስቲያኖ ሮናልዶን ይዛ ወደ ዓለም ዋንጫ የምትጓዘው የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት ምን ይመስላል?
የቀድሞ ኮከብ ፒተር ሽማይክልም የሮናልዶ አስተያየት ተረት ነው የመሰለኝ ማለቱ ተሰምቷል። የዩናይትድ ተከላካዩ ራፋይል ቫራን የሮናልዶ አስተያየት ሁሉንም የክለቡ ተጫዋቾች አውኳል ብሏል።
ጋሪ ኔቭልም የሮናልዶ ኮንትራት እንዲቋረጥ ከጠየቁ የቀድሞ የዩናይትድ ተጫዋቾች መካከል ይገኝበታል።
በኳታሩ የአለም ዋንጫ የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድንን በአምበልነት የሚመራው ሮናልዶ፥ ዝምታውን የሰበረበት ቃለመጠይቅ በአለም ዋንጫውም የመጨረሻው ተሳትፎው ላይ ጥቁር ጥላ አሳርፎበታል።
ሮናልዶ ለፒርስ ሞርጋን ምን አለ?
ፓርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በቶክ ቲቪ ከፔርስ ሞርጋን ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ስለክለቡና አሰልጣኙ ቴን ሀግ የተሰማውን ቅሬታ አንፀባርቋል።
"አሰልጣኙ ኤሪክ ቴን ሀግን አላከብረውም፤ ከክለቡ እንድወጣም የሚገፉኝ የክለቡ ሰዎች አሉ፤ የመከዳት ስሜት ተሰምቶኛል" ነበር ያለው።
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከለቀቁ በኋላ በክለቡ ለውጥ የለም ብሎ እንደሚያምንም ተናግሯል። ሮናልዶ ስለቀድሞ የክለብ ጓደኞቹ እና አሰልጣኞች የሰጠው አስተያየትም ከክለቡ እና ደጋፊዎች ጋር ቅራኔ ውስጥ ከቶታል።