ፓርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ "ተከድቻለሁ" አለ
ለአሰልጣኝ ቴን ሀግ ክብር የለኝም ያለው ሮናልዶ ስለ ክለቡ አመራሮች ያለውን አስተያየት በመግለፅ ዝምታውን ሰብሯል
ማንቸስተር ዩናይትድ የሚሰጠው ምላሽም እየተጠበቀ ነው
ፓርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ "ተከድቻለሁ" አለ።
ሮናልዶ በቶክ ቲቪ ከፔርስ ሞርጋን ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ዝምታውን ሰብሯል።
"አሰልጣኙ ኤሪክ ቴን ሀግ ብቻ ሳይሆን በክለቡ ሁለት ወይም ሶስት ሰዎች ከዩናይትድ እንድወጣ እየገፉኝ ነው፤ የመከዳት ስሜት ተሰምቶኛል" ብሏል የ37 አመቱ ተጫዋች።
የክለቡ አመራሮች ሊያሰናብቱህ ያስባሉ ወይ ተብሎ ሲጠየቅም "ግድ አይሰጠኝም፤ ሰዎች እውነቱን ሊሰሙ ይገባል፤ ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ባለፈው አመትም የተወሰኑ ሰዎች እንደማይፈልጉኝ ይሰማኛል" የሚል የሰነበተ ቅሬታውን ተናግሯል።
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከለቀቁ በኋላ በክለቡ ለውጥ የለም ያለው ሮናልዶ ከክለቡ እና ከደጋፊዎቹ ፀብ እንደሌለው ገልጿል።
ስለ ክለቡ የቀድሞ አሰልጣኝ ራልፍ ራኚክ ሲጠየቅም "አሰልጣኝ ሳይሆን ማንቸስተር ዩናይትድን ይይዛል እንዴ" ሲል ተሳልቆበታል።
የቀድሞ የክለብ አጋሩ ዋይኒ ሩኒ ፀባዩን እንዲያርም ለሰጠው አስተያየት ምላሽ ሲሰጥም "ሩኒ በዚህ ደረጃ ተበሳጭቶ ስለኔ አስተያየት መስጠቱ ገርሞኛል፤ ምናልባት እሱ ጨዋታ አቁሞ እኔ ግን ከፍ ባለ ደረጃ እየተጫወትኩ ስለሆነ ነው ይህን ያለው" ብሏል።
ሮናልዶ ለቴን ሀግ ምንም አይነት ክብር እንደሌለውም ነው የገለፀው።
ቀያዮቹ ሰይጣኖች በመስከረም ወር በአስቶንቪላ 3 ለ 1 ሲረቱ ሮናልዶ ባልተጠቀሰ ህመም ሳይሰለፍ ቀርቷል።
ከቶተንሃም ጋር ሲጫወቱም ተጠባባቂ አልሆንም ማለቱ ያበሳጫቸው ቴን ሀግ ባለፈው ወር ከቼልሲ ጋር ለነበራቸው ጨዋታ አልተጠቀሙበትም።
"ቴን ሀግ ለእኔ ምንም ክብር የለውም፤ እኔም የማያከብረኝን አላከብርም" ብሏል ስለ አሰልጣኙ ሲጠየቅ።
በሚያዚያ ወር ልጁን ማጣቱ ከባድ ሀዘን ላይ ጥሎት እንደነበር ጠቅሶም ሊቨርፑል ከዩናይትድ ሲጫወት የቀያዬቹ ደጋፊዎች ሀዘኑን በመጋራት ላሳዩት ድጋፍ አመስግኗል።
ሮናልዶ ያደረገው ቃለመጠይቅ የፊታችን ረቡዕ እና ሀሙስ ይቀርባል ተብሏል።
ሮናልዶ ከ340 በላይ ጨዋታዎች ላይ ለዩናይትድ ተሰልፎ ከ144 በላይ ጎሎችን አስቆጥሯል።
ለሪያል ማድሪድ 450 ለጁቬንቱስ ደግሞ 101 ጎሎችን ያስቆጠረው ግብ አዳኝ ወደ ዩናይትድ ዳግም ከተመለሰ በኋላ ግን የቀደመ ክህሎቱ ርቆታል።
የምወደው ክለቤ ከድቶኛል ያለው ፓርቹጋላዊ ከኳታሩ የአለም ዋንጫ መልስ ቀጣይ መዳረሻውን ሊያሳውቅ ይችላል ተብሏል።
በተጫዋቹ አስተያየት ዙሪያም ማንቸስተር ዩናይትድ የሚሰጠው ምላሽ እየተጠበቀ ነው።